ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 11:8-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. ብዙ ሰዎች ልበሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎች ደግሞ ለምለም የዛፍ ቅርንጫፍ እየቈረጡ ያነጥፉ ነበር።

9. ከፊቱ የቀደሙትና ከኋላው የተከተሉትም በታላቅ ድምፅ፤ እንዲህ ይሉ ነበር፤“ሆሣዕና!በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!

10. የምትመጣው የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት!ሆሣዕና በአርያም!”።

11. ኢየሱስም ኢየሩሳሌም ደረሰ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ በዙሪያው ያለውንም ሁሉ ተመለከተ፤ ቀኑም ስለመሸ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር ወደ ቢታንያ ወጣ።

12. በማግሥቱ ከቢታንያ ሲወጡ ኢየሱስ ተራበ።

13. እርሱም ቅጠል ያላት የበለስ ዛፍ ከሩቅ አየ፤ ምናልባት ፍሬ ይገኝባት እንደሆነ ብሎ ወደ እርሷ መጣ፤ ነገር ግን የበለስ ወራት አልነበረምና ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም።

14. ከዚያም ዛፏን፣ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ማንም ፍሬ ከአንቺ አይብላ” አላት። ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሲናገር ሰሙ።

15. ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ፣ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያስወጣ ጀመር። የገንዘብ መንዛሪዎችን ጠረጴዛና የርግብ ሻጮችን መቀመጫ ገለባበጠ፤

16. ማንም ዕቃ ተሸክሞ በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳያልፍ ከለከለ።

17. ሲያስተምራቸውም፣ “ ‘ቤቴ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ አልተጻፈምን? እናንተ ግን የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት!” አላቸው።

18. የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም፣ ይህን ሲሰሙ እንዴት እንደሚያጠፉት መንገድ ይፈልጉ ጀመር፤ ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ በመገረማቸው ፈርተውታልና።

19. በመሸም ጊዜ ከከተማዪቱ ወጥተው ሄዱ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማርቆስ 11