ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 10:19-37 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

19. ትእዛዛትን ታውቃለህ፤ አትግደል፤ አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አታታልል፤ አባትህንና እናትህን አክብር።”

20. ሰውየውም፣ “መምህር ሆይ፤ እነዚህን ሁሉ ከልጅነቴ ጀምሮ ጠብቄአለሁ” አለው።

21. ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው፤ “እንግዲያው አንድ ነገር ይጐድልሃል፤ ሂድና ያለህን ሁሉ ሽጥ፤ ለድኾችም ስጥ፤ በሰማይ የተከማቸ ሀብት ታገኛለህ፤ ከዚያ በኋላ ና፤ ተከተለኝም” አለው።

22. ሰውየው ይህን ሲሰማ ክፉኛ አዘነ፤ ብዙ ሀብት ስለ ነበረውም እየተከዘ ሄደ።

23. ኢየሱስ ዙሪያውን በመመልከት ደቀ መዛሙርቱን፣ “ለሀብታሞች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ከባድ ነገር ነው!” አላቸው።

24. ደቀ መዛሙርቱም በንግግሩ ተገረሙ፤ ኢየሱስ ግን እንደ ገና መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ልጆች ሆይ፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ከባድ ነገር ነው!

25. ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀለዋል።”

26. ደቀ መዛሙርቱም ይበልጥ በመገረም፣ “ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?” ተባባሉ።

27. ኢየሱስም አያቸውና፣ “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላል” አላቸው።

28. ጴጥሮስም፣ “እነሆ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ” አለው።

29. ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ሲል ቤቱን ወይም ወንድሞቹን ወይም እኅቶቹን ወይም እናቱን ወይም አባቱን ወይም ልጆቹን ወይም ዕርሻውን የተወ ሁሉ፣

30. አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እኅቶችን፣ እናቶችን፣ ልጆችንና ዕርሻን መቶ ዕጥፍ የማይቀበል፣ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይወርስ የለም።

31. ነገር ግን ብዙ ፊተኞች የሆኑ ኋለኞች፣ ኋለኞች የሆኑም ፊተኞች ይሆናሉ።”

32. ወደ ኢየሩሳሌም ለመውጣት በመንገድ ላይ ሳሉ፣ ኢየሱስ ፊት ፊታቸው ይሄድ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ተገረሙ፣ ሌሎች የተከተሉት ደግሞ ፈርተው ነበር። ደግሞም ዐሥራ ሁለቱን ከሕዝቡ ለይቶ ምን እንደሚደርስበት ነገራቸው፤

33. እንዲህም አላቸው፤ “ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም የሞት ፍርድ ይፈርዱበታል፤ አሳልፈው ለአሕዛብ ይሰጡታል፤

34. ያፌዙበታል፤ ይተፉበታል፣ ይገርፉታል፣ ከዚያም ይገድሉታል፤ እርሱ ግን ከሦስት ቀን በኋላ ይነሣል።”

35. ከዚያም የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “መምህር ሆይ፤ የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንፈልጋለን” አሉት።

36. እርሱም፣ “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው።

37. እነርሱም፣ “በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝህ፣ አንዳችን በግራህ እንድንቀመጥ ፍቀድልን” አሉት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማርቆስ 10