ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 7:11-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. “በዚያ ጊዜም በግብፅና በከነዓን አገር ሁሉ፣ ታላቅ መከራን ያስከተለ ራብ መጣ፤ አባቶቻችንም የሚበሉትን አጡ።

12. ያዕቆብም እህል በግብፅ መኖሩን በሰማ ጊዜ፣ አባቶቻችንን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ግብፅ ላካቸው፤

13. ለሁለተኛ ጊዜ ሲሄዱ ደግሞ ዮሴፍ ማንነቱን ለወንድሞቹ ገለጠ፤ ፈርዖንም ስለ ዮሴፍ ዘመዶች ተረዳ።

14. ከዚህ በኋላ፣ ዮሴፍ ልኮ አባቱን ያዕቆብንና ሰባ አምስት ነፍስ የሚሆኑ ቤተ ዘመዶቹን በሙሉ አስመጣ።

15. ያዕቆብ ወደ ግብፅ ወረደ፤ እርሱም አባቶቻችንም በዚያ ሞቱ።

16. አስከሬናቸውም ወደ ሴኬም ተወስዶ፣ አብርሃም ከዔሞር ልጆች ላይ በጥሬ ብር በገዛው መቃብር ተቀበረ።

17. “እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባው ቃል የሚፈጸምበት ጊዜ ሲቃረብም፣ በግብፅ የነበረው የሕዝባችን ቍጥር እየበዛ ሄደ።

18. ከዚያ በኋላ ዮሴፍን የማያውቅ ሌላ ንጉሥ በግብፅ ነገሠ።

19. እርሱም ሕዝባችንን በተንኰሉ አስጨነቀ፤ ገና የተወለዱ ሕፃናታቸውም ይሞቱ ዘንድ ወደ ውጭ አውጥተው እንዲጥሏቸው አስገደዳቸው።

20. “በዚህ ጊዜ ሙሴ ተወለደ፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ያገኘ ውብ ሕፃን ነበር። በአባቱም ቤት ሦስት ወር በእንክ ብካቤ አደገ።

21. ወደ ውጭ በተጣለም ጊዜ የፈርዖን ልጅ አግኝታ ወሰደችው፤ እንደ ራሷ ልጅ አድርጋም አሳደገችው።

22. ሙሴም የግብፆችን ጥበብ ሁሉ ተማረ፤ በንግግሩና በተግባሩም ብርቱ ሆነ።

23. “ሙሴ አርባ ዓመት በሆነው ጊዜ፣ ወንድሞቹን የእስራኤልን ልጆች ሊጐበኝ በልቡ አሰበ።

24. እርሱም፣ አንድ ግብፃዊ ከወገኖቹ አንዱን በደል ሲያደርስበት አይቶ ግብፃዊውንም ገደለ፤ ለተገፋው ወገኑም ተበቀለ።

25. ወገኖቹም እግዚአብሔር በእርሱ እጅ ነጻ እንደሚያወጣቸው የሚያሰተውሉ መስሎት ነበር፤ እነርሱ ግን አላስተዋሉም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 7