ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 7:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ሊቀ ካህናቱም፣ “ይህ የቀረበብህ ክስ እውነት ነውን?” አለው።

2. እስጢፋኖስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ወንድሞችና አባቶች ሆይ፤ አድምጡኝ! አባታችን አብርሃም ወደ ካራን ከመምጣቱ በፊት፣ ገና በመስጴጦምያ ሳለ፣ የክብር አምላክ ተገልጦለት፤

3. ከአገርህና ከወገንህ ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ አለው።

4. “እርሱም ከከለዳውያን ምድር ወጥቶ በካራን ተቀመጠ። ከአባቱም ሞት በኋላ፣ አሁን እናንተ ወደምትኖሩበት ወደዚህ አገር አመጣው።

5. በዚህም ስፍራ አንዲት ጫማ ታህል እንኳ ርስት አልሰጠውም፤ ነገር ግን በዚያን ጊዜ ምንም ልጅ ሳይኖረው፣ እርሱና ከእርሱም በኋላ ዘሩ ምድሪቱን እንደሚወርሱ እግዚአብሔር ቃል ገባለት።

6. ደግሞም እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናገረው፤ ‘ዘርህ በባዕድ አገር መጻተኛ ይሆናል፤ አራት መቶ ዓመትም በባርነት ቀንበር ሥር ይማቅቃል።

7. ሆኖም በባርነት የሚገዛቸውን ሕዝብ እኔ ደግሞ እቀጣዋለሁ። ከዚያም አገር ወጥተው በዚህች ስፍራ ያመልኩኛል።’

8. ከዚያም የግዝረትን ኪዳን ሰጠው፤ አብርሃምም ይስሐቅን ወለደ፤ በስምንተኛውም ቀን ገረዘው። ይስሐቅም ያዕቆብን ወለደ፤ ያዕቆብም ዐሥራ ሁለቱን የነገድ አባቶች ወለደ።

9. “የነገድ አባቶችም በዮሴፍ ቀንተው በባርነት ወደ ግብፅ ሸጡት፤ እግዚአብሔር ግን ከእርሱ ጋር ስለ ነበር፣

10. ከመከራው ሁሉ አወጣው፤ በግብፅም ንጉሥ በፈርዖን ፊት ሞገስና ጥበብን አጐናጸፈው፤ ፈርዖንም በግብፅና በቤተ መንግሥቱ ሁሉ ላይ ኀላፊ አድርጎ ሾመው።

11. “በዚያ ጊዜም በግብፅና በከነዓን አገር ሁሉ፣ ታላቅ መከራን ያስከተለ ራብ መጣ፤ አባቶቻችንም የሚበሉትን አጡ።

12. ያዕቆብም እህል በግብፅ መኖሩን በሰማ ጊዜ፣ አባቶቻችንን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ግብፅ ላካቸው፤

13. ለሁለተኛ ጊዜ ሲሄዱ ደግሞ ዮሴፍ ማንነቱን ለወንድሞቹ ገለጠ፤ ፈርዖንም ስለ ዮሴፍ ዘመዶች ተረዳ።

14. ከዚህ በኋላ፣ ዮሴፍ ልኮ አባቱን ያዕቆብንና ሰባ አምስት ነፍስ የሚሆኑ ቤተ ዘመዶቹን በሙሉ አስመጣ።

15. ያዕቆብ ወደ ግብፅ ወረደ፤ እርሱም አባቶቻችንም በዚያ ሞቱ።

16. አስከሬናቸውም ወደ ሴኬም ተወስዶ፣ አብርሃም ከዔሞር ልጆች ላይ በጥሬ ብር በገዛው መቃብር ተቀበረ።

17. “እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባው ቃል የሚፈጸምበት ጊዜ ሲቃረብም፣ በግብፅ የነበረው የሕዝባችን ቍጥር እየበዛ ሄደ።

18. ከዚያ በኋላ ዮሴፍን የማያውቅ ሌላ ንጉሥ በግብፅ ነገሠ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 7