ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 5:10-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. እርሷም ወዲያውኑ እግሩ ሥር ወድቃ ሞተች፤ ጒልማሶቹም ሲገቡ ሞታ አገኟት፤ አውጥተውም በባሏ አጠገብ ቀበሯት።

11. መላዪቱን ቤተ ክርስቲያንና ይህን የሰሙትን ሁሉ፣ ታላቅ ፍርሀት ያዛቸው።

12. ሐዋርያትም በሕዝቡ መካከል ብዙ ታምራዊ ምልክቶችንና ድንቅ ሥራዎችን አደረጉ፤ አማኞቹም ሁሉ ‘የሰሎሞን ደጅ’ በተባለው መመላለሻ ይሰበሰቡ ነበር።

13. ከእነርሱ ጋር ሊቀላቀል የደፈረ ማንም አልነበረም፤ ሆኖም ሕዝቡ እጅግ ያከብሯቸው ነበር፤

14. ብዙ ወንዶችና ሴቶችም ከጊዜ ወደ ጊዜ በጌታ እያመኑ ወደ እነርሱ ይጨመሩ ነበር።

15. ከዚህም የተነሣ፣ ጴጥሮስ በዚያ ሲያልፍ፣ ቢያንስ ጥላው እንኳ በጥቂቶች ላይ እንዲያርፍባቸው በማለት ሕመምተኞችን ወደ ውጭ እያወጡ በዐልጋና በቃሬዛ በመንገድ ላይ ያስተኙ ነበር።

16. በኢየሩሳሌም አካባቢ ከሚገኙ ከተሞች፣ ሕመምተኞችንና በርኵሳን መናፍስት የሚሠቃዩትን ይዘው የሚመጡት ሰዎች አካባቢውን ያጨናንቁት ነበር፤ የመጡትም ሁሉ ይፈወሱ ነበር።

17. ከዚህም የተነሣ ሊቀ ካህናቱና አብረውት የነበሩት የሰዱቃውያን ወገን ሁሉ በቅናት ተሞሉ፤

18. ሐዋርያትንም ይዘው ማረፊያ ቤት ከተቷቸው።

19. ይሁን እንጂ የጌታ መልአክ በሌሊት የእስር ቤቱን ደጆች ከፍቶ አወጣቸውና፣

20. “ሂዱ፤ በቤተ መቅደሱም አደባባይ ቁሙ፤ የዚህንም ሕይወት ቃል ሁሉ ለሕዝብ ንገሩ” አላቸው።

21. እንደ ነጋም፣ በተነገራቸው መሠረት፣ ወደ ቤተ መቅደሱ አደባባይ ገብተው ሕዝቡን ማስተማር ጀመሩ።ሊቀ ካህናቱና ከእርሱ ጋር የነበሩት መጥተው የአይሁድን ሸንጎና የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጉባኤ በሙሉ በአንድነት ሰበሰቡ፤ ሐዋርያትንም እንዲያመጡ ሰዎችን ወደ እስር ቤት ላኩ።

22. የተላኩትም ወደ እስር ቤቱ ሄደው በዚያ አላገኟቸውም፤ ተመልሰውም እንዲህ አሏቸው፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 5