ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 27:21-38 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. ሰዎቹ እህል ሳይቀምሱ ብዙ ቀን ከቈዩ በኋላ፣ ጳውሎስ በመካከላቸው ቆሞ እንዲህ አለ፤ “እናንት ሰዎች ሆይ፤ የነገርኋችሁን ሰምታችሁ ቢሆን ኖሮ፣ ከቀርጤስ ባልተነ ሣችሁና ይህ ጒዳትና ጥፋት ባልደረሰባችሁ ነበር።

22. አሁንም ቢሆን አይዟችሁ መርከቧ እንጂ ከእናንተ አንዲት ነፍስ እንኳ አትጠፋምና።

23. በትላንትናዋ ሌሊት፣ የእርሱ የሆንሁትና የማመልከው እግዚአብሔር የላከው መልአክ በአጠገቤ ቆሞ፣

24. ‘ጳውሎስ ሆይ፤ አትፍራ፤ በቄሳር ፊት መቆም ይገባሃል፤ ከአንተ ጋር የሚጓዙትንም ሰዎች ሕይወት እግዚአብሔር አትርፎልሃል’ አለኝ።

25. ስለዚህ፣ እናንት ሰዎች ሆይ፤ አይዞአችሁ እርሱ እንደ ነገረኝ እንደዚያው እንደሚሆን በእግዚአብሔር አምናለሁና።

26. ይሁን እንጂ፣ ወደ አንዲት ደሴት በነፋስ ተወስደን እዚያ መጣላችን አይቀርም።”

27. በዐሥራ አራተኛው ሌሊት በአድርያ ባሕር ላይ ከወዲያ ወዲህ ስንገላታ፣ እኩለ ሌሊት ገደማ መርከበኞቹ ወደ መሬት የተቃረቡ መሰላቸው፤

28. የጥልቀት መለኪያውን ገመድ ወደ ታች ጥለው ሲመለከቱት የውሃው ጥልቀት አርባ ሜትር ያህል ሆኖ አገኙት፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላም ደግመው ሲጥሉ ጥልቀቱ፣ ሠላሳ ሜትር ያህል ሆነ።

29. ከቋጥኞቹም ጋር እንዳንላተም በመፍራት፣ አራት መልሕቆች ከመርከቡ በስተ ኋላ ጣሉ፤ ምነው በነጋ እያሉም ይለምኑ ነበር።

30. መርከበኞቹም ከመርከቡ በስተ ፊት መልሕቅ የሚጥሉ መስለው፣ ትንሿን ጀልባ በማውረድ ከመርከቧ ሊያመልጡ ሞከሩ።

31. ጳውሎስም የመቶ አለቃውንና ወታደሮቹን፣ “እነዚህ ሰዎች መርከቡ ላይ ካልቈዩ እናንተም ልትተርፉ አትችሉም” አላቸው።

32. በዚህ ጊዜ ወታደሮቹ ገመዶቹን ቈርጠው ትንሿ ጀልባ ባሕሩ ላይ ተንሳፋ እንድትቀር ለቀቋት።

33. ልክ ሊነጋጋ ሲል፣ ጳውሎስ ሁሉም ምግብ እንዲበሉ እንዲህ ሲል ለመናቸው፤ “ዐሥራ አራት ቀን ሙሉ ልባችሁ ተንጠልጥሎ ምንም ሳትቀምሱ ጦማችሁን ሰነበታችሁ፤

34. ስለዚህ ስለሚያበረታችሁ አሁን እህል እንድትቀምሱ እለምናችኋላሁ፤ ከእናንተ መካከል ከራሱ ጠጒር አንዲት እንኳ የሚነካበት ማንም የለምና።”

35. ይህን ካለ በኋላም፣ እንጀራ ይዞ በሁሉም ፊት እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ቈርሶም ይበላ ጀመር።

36. ሁሉም ተበራቱና እንጀራውን ራሳቸው ወስደው በሉ።

37. በመርከቡም ላይ በአጠቃላይ ሁለት መቶ ሰባ ስድስት ሰዎች ነበርን።

38. በልተውም ከጠገቡ በኋላ ስንዴውን ወደ ባሕር በመጣል የመርከቡን ክብደት አቃለሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 27