ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 27:10-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. “እናንት ሰዎች፤ ጒዞው አደገኛ እንደሚሆን፣ በመርከቡና በጭነቱ እንዲሁም በእኛ በራሳችን ላይ እንኳ ትልቅ ጒዳት እንደሚደርስ ይታየኛል” ብሎ አስጠነቀቃቸው።

11. የመቶ አለቃው ግን ከጳውሎስ ምክር ይልቅ የመርከቡ መሪና የመርከቡ ባለቤት ያሉትን ይሰማ ነበር።

12. ክረምቱንም በዚያ ለማሳለፍ ወደቡ አመቺ ስላልነበረ፣ አብዛኛዎቹ ፍንቄ ወደተባለው ወደብ ደርሰው በዚያ ለመክረም ተስፋ በማድረግ ጒዞአችንን እንድንቀጥል ውሳኔ አስተላለፉ፤ ወደቡም በቀርጤስ ደቡብ ምዕራብና ሰሜን ምዕራብ ትይዩ የሚገኝ ነበር።

13. መጠነኛ የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜም እንዳሰቡት የሆነላቸው መስሎአቸው መልሕቁን ነቅለው፣ የቀርጤስን ዳርቻ በመያዝ ተጓዙ።

14. ብዙም ሳይቈይ ግን፣ ‘ሰሜናዊ ምሥራቅ’ የሚሉት ኀይለኛ ዐውሎ ነፋስ ከደሴቲቱ ተነሥቶ ቍልቍል መጣባቸው።

15. መርከቢቱም በማዕበሉ ስለ ተያዘች፣ ወደ ነፋሱ ልትገፋ አልቻለችም፤ ስለዚህ መንገድ ለቀን በነፋሱ ተነዳን።

16. ቄዳ የተባለችውን ትንሽ ደሴት ተገን አድርገን በማለፍ፣ የመርከቧን ሕይወት አድን ጀልባ በብዙ ድካም ለማትረፍ ቻልን፤

17. ጀልባዋንም ወደ ላይ ጐትተው ካወጧት በኋላ መርከቧ እንዳትፈራርስ ዙሪያዋን በገመድ ጠምጥመው አሰሯት፤ ስርቲስ ከተባለው አሸዋማ ደለል ጋር ሄደው እንዳይላተሙ ስለ ፈሩም፣ የመርከቧን ሸራ አውርደው እንዲሁ በዘፈቀደ እንድትነዳ አደረጉ።

18. ማዕበሉም ክፉኛ ስላንገላታን፣ በማግስቱ ጭነቱን እያነሡ ወደ ባሕር ይጥሉ ጀመር፤

19. በሦስተኛውም ቀን፣ የመርከቧን ሸራ ማውጫና ማውረጃ መሣሪያ በገዛ እጃቸው ነቃቅለው ወደ ባሕር ጣሉት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 27