ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 25:8-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. ጳውሎስም፣ “እኔ በአይሁድም ሕግ ሆነ በቤተ መቅደሱ ወይም በቄሣር ላይ የፈጸምሁት በደል የለም” ሲል የመከላከያ መልሱን ሰጠ።

9. ፊስጦስም ለአይሁድ በጎ ለመዋል ፈልጎ፣ ጳውሎስን “ስለዚህ ጒዳይ ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተህ በእኔ ፊት ለመፋረድ ፈቃደኛ ነህን?” አለው።

10. ጳውሎስም እንዲህ አለ፤ “አሁንም ቢሆን ፍትሕ ማግኘት በምችልበት፣ በቄሳር ፍርድ ወንበር ፊት ቆሜአለሁ፤ አንተ ራስህ በሚገባ እንደምታውቀው በአይሁድ ላይ ምንም በደል አልፈጸምሁም፤

11. ይሁን እንጂ ለሞት የሚያበቃ በደል ከተገኘብኝ፣ አልሙት አልልም፤ እነዚህ አይሁድ የሚያቀርቡብኝ ክስ እውነት ካልሆነ ግን፣ እኔን ለእነርሱ አሳልፎ ሊሰጥ የሚችል የለም፤ ወደ ቄሳር ይግባኝ ብያለሁ።”

12. ፊስጦስ ከመማክርቱ ጋር ከተመካከረ በኋላ፣ “ወደ ቄሳር ይግባኝ ስላልህ፣ ወደ ቄሳር ትሄዳለህ” አለው።

13. ከጥቂት ቀንም በኋላ፣ ንጉሥ አግሪጳና በርኒቄ ፊስጦስን እጅ ሊነሡ ወደ ቂሳርያ ወረዱ፤

14. በዚያም ብዙ ቀን ተቀመጡ፤ ፊስጦስም የጳውሎስን ጒዳይ አንሥቶ ለንጉሡ እንዲህ አለው፤ “ፊልክስ በእስር ቤት የተወው አንድ ሰው እዚህ አለ፤

15. ወደ ኢየሩሳሌም በሄድሁ ጊዜ፣ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሽማግሌዎች እንድፈርድበት ከሰውት ነበር።

16. “እኔም፣ ተከሳሽ በከሳሾቹ ፊት ቆሞ ለተከሰሰበት ነገር መልስ ለመስጠት ዕድል ሳያገኝ፣ አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ልማድ እንዳልሆነ ነገርኋቸው።

17. ስለዚህ ከሳሾቹ ከእኔ ጋር ወደዚህ በመጡ ጊዜ፣ ጒዳዩን ሳላጓትት በማግስቱ ችሎት ተቀምጬ ያን ሰው እንዲያቀርቡት አዘዝሁ።

18. ከሳሾቹም ተነሥተው በመቆም ሲናገሩ፣ እኔ ያሰብሁትን ያህል ከባድ ክስ አላቀረ ቡበትም፤

19. ይልቁን ስለ ገዛ ሃይማኖታቸውና ሞቶ ስለ ነበረው፣ ጳውሎስ ግን ሕያው ነው ስለሚለው ሰው፣ ስለ ኢየሱስ ይከራከሩት ነበር።

20. እኔም ይህን ነገር እንዴት እንደምፈታው ግራ ስለገባኝ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ስለ ዚሁ ጒዳይ እንዲፋረድ ፈቃደኝነቱን ጠየቅሁት።

21. ነገር ግን ጳውሎስ ጒዳዩ በንጉሠ ነገሥቱ እንዲታይለት ይግባኝ ባለ ጊዜ፣ እኔም ወደ ቄሳር እስከምልከው ድረስ እስር ቤት እንዲይ አዘዝሁ።”

22. አግሪጳም ፊስጦስን፣ “እኔም እኮ ይህ ሰው ሲናገር መስማት እፈልግ ነበር” አለው።እርሱም፣ “እንግዲያውስ ነገ ትሰማዋለህ” አለው።

23. በማግስቱም አግሪጳና በርኒቄ በታላቅ ክብር መጥተው፣ ከከፍተኛ መኰንኖችና ከከተማዪቱ ታላላቅ ሰዎች ጋር ወደ መሰብሰቢያው አዳራሽ ገቡ፤ በፊስጦስም ትእዛዝ ጳውሎስ እንዲቀርብ ተደረገ።

24. በዚህ ጊዜ ፊስጦስ እንዲህ አለ፤ “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፤ እንዲሁም እዚህ አብራችሁን ያላችሁ ሁሉ፤ ይህን ሰው ታዩታላችሁ? በኢየሩሳሌምና እዚህ በቂሳርያም የሚኖሩ አይሁድ ሁሉ፣ ይህ ሰው ከእንግዲህ በሕይወት መኖር አይገባውም በማለት እየጮኹ ለመኑ።

25. እኔም ለሞት የሚያበቃ አንዳች ነገር አለ ማድረጉን ተረዳሁ፤ ሆኖም ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ይግባኝ በማለቱ ወደ ሮም ልልከው ወሰንሁ።

26. ነገር ግን ስለ እርሱ ወደ ጌታዬ የምጽፈው የተረጋገጠ ነገር አላገኘሁም፤ ስለዚህም ከተመረመረ በኋላ የምጽፈውን ነገር ለማግኘት ሁላችሁም ፊት በተለይ ደግሞ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፤ በአንተ ፊት አቀረብሁት፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 25