ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 22:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. “ወንድሞችና አባቶች ሆይ፤ አሁን የማቀርብላችሁን የመከላከያ መልሴን ስሙኝ።”

2. እነርሱም በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲናገር በሰሙ ጊዜ ከፊት ይልቅ ጸጥ አሉ።ጳውሎስም እንዲህ አለ፤

3. “እኔ በኪልቅያ በምትገኘው በጠርሴስ የተወለድሁ አይሁዳዊ ስሆን፣ ያደግሁት ግን በዚህ ከተማ ነው። የአባቶቻችንን ሕግ በገማልያል እግር ሥር ተቀምጬ በሚገባ ተምሬአለሁ፤ ዛሬ እናንተ እንዲህ የምትቀኑለትን ያህል እኔም ለእግዚአብሔር እቀና ነበር።

4. ይህን መንገድ የሚከተሉትንም እስከ ሞት ድረስ እያሳደድሁ፣ ወንዶችንም ሴቶችንም አስሬ ወደ ወህኒ እጥላቸው ነበር።

5. ይህን ተግባሬን ሊቀ ካህናቱም ሆነ ሸንጎው ሁሉ ሊመሰክሩ ይችላሉ። ከእነርሱ ደብዳቤ ተቀብዬ ደማስቆ ወዳሉት ወንድሞቻቸው በመሄድ፣ እነዚህን ሰዎች አሳስሬ ወደ ኢየሩሳሌም አምጥቼ ለማስቀጣት ወደዚያ እሄድ ነበር።

6. “ስንጓዝም እኩለ ቀን ገደማ ወደ ደማስቆ እንደ ተቃረብሁ፣ ድንገት ታላቅ ብርሃን ከሰማይ በዙሪያዬ በራ፤

7. እኔም ምድር ላይ ወደቅሁ፤ ከዚያም፣ ‘ሳውል፤ ሳውል፤ ለምን ታሳድደኛለህ?’ የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ።

8. “እኔም፣ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተ ማን ነህ?’ አልሁት።“እርሱም፣ ‘አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ’ አለኝ።

9. ከእኔ ጋር የነበሩትም ብርሃኑን አዩ፤ ነገር ግን የሚናገረኝን የእርሱን ድምፅ በትክክል አልሰሙም።

10. “እኔም፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ምን ላድርግ?’ አልሁት።“ጌታም፣ ‘ተነሥተህ ወደ ደማስቆ ሂድ፤ በዚያም ልታደርገው የሚገባህን ሁሉ ይነግሩሃል’ አለኝ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 22