ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 21:7-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. ከጢሮስ ተነሥተን ጒዞአችንን በመቀጠል ጴጤሌማይስ ደረስን፤ ከመርከብ ወርደንም ለወንድሞች ሰላምታ ካቀረብን በኋላ፣ አንድ ቀን ከእነርሱ ጋር ቈየን።

8. በማግስቱ ከዚያ ተነሥተን ቂሳርያ ደረስን፤ ከሰባቱ ወንጌላውያን አንዱ በሆነው በፊልጶስ ቤትም ዐረፍን።

9. እርሱም ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት።

10. በዚያም ብዙ ቀን ከተቀመጥን በኋላ አጋቦስ የተባለ ነቢይ ከይሁዳ ወረደ፤

11. ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ ወሰደ፤ የራሱንም እጅና እግር በማሰር፣ “መንፈስ ቅዱስ፣ ‘በኢየሩሳሌም ያሉ አይሁድ የዚህን መታጠቂያ ባለቤት እንዲህ አድርገው በማሰር ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል’ ይላል” አለ።

12. ይህን ስንሰማ እኛና በዚያም የሚኖሩት ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ለመነው።

13. ጳውሎስ ግን፣ “ለምን እንዲህ እያለቀሳችሁ ልቤን ታባቡታላችሁ? እኔ መታሰር ቀርቶ ስለ ጌታ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳን ዝግጁ ነኝ” አላቸው።

14. ምክራችንን አልቀበል ስላለን፣ “እንግዲህ የጌታ ፈቃድ ይሁን” ብለን ተውነው።

15. ከዚህ በኋላ፣ ተዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም ወጣን።

16. በቂሳርያ ከነበሩት ደቀ መዛሙርትም አንዳንዶቹ ወደ ምናሶን ቤት ይዘውን መጡ፤ እኛም በዚያው ተቀመጥን። ምናሶን የቆጵሮስ ሰው ሲሆን፣ ከመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት አንዱ ነበረ።

17. ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜ፣ ወንድሞች በደስታ ተቀበሉን።

18. በማግስቱም ጳውሎስና ሌሎቻችንም ያዕቆብን ለማየት ሄድን፤ ሽማግሌዎችም ሁሉ በዚያ ነበሩ።

19. ጳውሎስም ሰላምታ ካቀረበላቸው በኋላ፣ እግዚአብሔር በእርሱ አገልግሎት አማካይነት በአሕዛብ መካከል ያደረገውን ሁሉ በዝርዝር አስረዳቸው።

20. እነርሱም ይህን ሲሰሙ፣ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ጳውሎስንም እንዲህ አሉት፤ “ወንድም ሆይ፤ በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ አይሁድ እንዳመኑ ተመልከት፤ ሁሉም ደግሞ ለሙሴ ሕግ የሚቀኑ ናቸው።

21. በአሕዛብ መካከል የሚኖሩ አይሁድ ሁሉ ሙሴን እንዲተዉና ልጆቻቸውን እንዳይገርዙ፣ በቈየው ልማዳችን መሠረት እንዳይኖሩ እንደምታስተምር ስለ አንተ ተነግሮአቸዋል።

22. መምጣትህን መስማታቸው የማይቀር ነውና፣ እንግዲህ ምን እናድርግ?

23. ስለዚህ የምንልህን አድርግ። ስእለት ያለባቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 21