ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 2:20-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. ታላቅና ክቡር የሆነው የጌታ ቀን ከመምጣቱ በፊት፣ፀሓይ ወደ ጨለማ፣ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ።

21. የጌታን ስም፣የሚጠራ ሁሉ ይድናል።’

22. “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ ይህን ቃል ስሙ፤ እናንት ራሳችሁ እንደምታውቁት፣ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ታምራትን፣ ድንቅ ነገሮችንና ምልክቶችን በእርሱ በኩል በማድረግ ለናዝሬቱ ኢየሱስ መስክሮለታል።

23. እግዚአብሔር በጥንት ውሳኔውና በቀደመው ዕውቀቱ ይህን ሰው አሳልፎ በእጃችሁ ሰጣችሁ፤ እናንተም በክፉ ሰዎች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት።

24. እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አስወግዶ አስነሣው፤ ሞት ይዞ ሊያስቀረው አልቻለምና።

25. ዳዊትም ስለ እርሱ እንዲህ ይላል፤“ ‘ጌታን ሁል ጊዜ በፊቴ አየዋለሁ፤እርሱ በቀኜ ነውና፣ከቶ አልታወክም።

26. ስለዚህ ልቤ ደስ አለው፤ አንደበቴም ሐሤት አደረገ፤ሥጋዬም በተስፋ ይኖራል።

27. ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፤ቅዱስህም መበስበስን እንዲያይ አታደርግም።

28. የሕይወትን መንገድ እንዳውቅ አደረግኸኝ፤በፊትህም በሐሤት ትሞላኛለህ።’

29. “ወንድሞች ሆይ፤ ከቀደምት አባቶች ዳዊት ሞቶ እንደ ተቀበረ፣ መቃብሩም እስከ ዛሬ ድረስ በመካከላችን እንደሚገኝ በድፍረት መናገር እችላለሁ።

30. ነቢይ በመሆኑም፣ እግዚአብሔር ከዘሮቹ አንዱን በዙፋኑ ላይ እንደሚያስቀምጥ በመሐላ ቃል የገባለት መሆኑን ዐወቀ።

31. ይህንን አስቀድሞ በማየቱ እርሱ በሲኦል እንደማይቀርና ሥጋውም እንደማይበሰብስ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ተናገረ።

32. ይህን ኢየሱስ፣ እግዚአብሔር ከሞት አስነሣው፤ እኛም ሁላችን ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን።

33. ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ካለ በኋላ፣ የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ከአብ ተቀብሎ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 2