ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 19:23-40 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

23. በዚህ ጊዜ፣ ስለ ጌታ መንገድ ታላቅ ሁከት ተፈጠረ።

24. ድሜጥሮስ የተባለ አንድ የብር አንጥረኛ የአርጤምስን ቤተ መቅደስ ምስሎች ከብር ቀጥቅጦ እየሠራ ለሠራተኞቹ የሚያስገኘው ገቢ ቀላል አልነበረም።

25. እርሱም እነዚህን ሠራተኞችና በተመሳሳይ ሙያ የሚተዳደሩትን ሌሎቹን ሰዎች በአንድነት ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፤ “ሰዎች ሆይ፤ ይህ ሥራ ጥሩ ገቢ እንደሚያስገኝልን ታውቃላችሁ።

26. ይህ ጳውሎስ የተባለ ሰው በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን፣ በመላው የእስያ አውራጃ የሚገኘውን በርካታ ሕዝብ እያሳመነ እንዳሳታቸው ይኸው የምታዩትና የምትሰሙት ነገር ነው፤ በሰው እጅ የተሠሩ አማልክት በፍጹም አማልክት እንዳልሆኑ ይናገራልና።

27. የዚህ የሥራችን መልካም ስም ከመጒደፉም በላይ፣ መላው እስያና ዓለም የሚያመልካት የታላቋ አርጤምስ ቤተ መቅደስም ዋጋ ቢስ ይሆናል፤ ደግሞም ገናናው ክብሯ ይዋረዳል።”

28. ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ ክፉኛ ተቈጥተው፣ “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉ ይጮኹ ጀመር።

29. ወዲያውም በከተማው ሁሉ ሁከት ተነሣ፤ ሕዝቡም አንድ ላይ በማበር የመቄዶንያ ተወላጅ የሆኑትንና ከጳውሎስ ጋር ይጓዙ የነበሩትን ጓደኞቹን፣ ጋይዮስንና አርስጥሮኮስን ይዘው ወደ ጨዋታ ማሳያው ስፍራ እየሮጡ ገቡ።

30. ጳውሎስም ወጥቶ ሕዝቡ ፊት ለመቅረብ ፈልጎ ነበር፤ ደቀ መዛሙርት ግን ከለከሉት።

31. ከአውራጃው ባለ ሥልጣኖች አንዳንድ ወዳጆቹ እንኳ፣ ጳውሎስ ወደ ጨዋታ ማሳያው ስፍራ ደፍሮ እንዳይገባ ሰው ልከው ለመኑት።

32. ጉባኤውም ተበጣብጦ፣ አንዱ አንድ ነገር ሲናገር ሌላውም ሌላ እየተናገረ ይጯጯኽ ነበር፤ አብዛኛውም ሰው ለምን እዚያ እንደ ተሰበሰበ እንኳ አያውቅም ነበር።

33. አይሁድም እስክንድሮስን ከሕዝቡ መካከል ገፍተው ወደ ፊት ባወጡት ጊዜ፤ አንዳንዶቹ እንዲናገርላቸው ጮኹ፤ እርሱም ሊከራከርላቸው ፈልጎ ዝም እንዲሉ በምልክት ጠቀሳቸው።

34. ነገር ግን እርሱ አይሁዳዊ መሆኑን ባወቁ ጊዜ ሁሉም በአንድ ድምፅ፣ “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት” እያሉ ሁለት ሰዓት ያህል ጮኹ።

35. የከተማዪቱም ዋና ጸሓፊ ሕዝቡን ጸጥ አሰኝቶ እንዲህ አለ፤ “የኤፌሶን ሰዎች ሆይ፤ የታላቋ የአርጤምስ ቤተ መቅደስና ከሰማይ የወረደው ምስሏ ጠባቂ የኤፌሶን ከተማ ሕዝብ መሆኑን የማያውቅ ማን አለ?

36. ስለዚህ፣ ይህ ሐቅ የማይካድ እንደ መሆኑ መጠን፣ ልትረጋጉና አንዳች ነገር በጥድፊያ ከመፈጸም ልትጠቡ ይገባችኋል።

37. እነዚህን ሰዎች ቤተ መቅደስን ሳይዘርፉ ወይም አምላካችን በሆነችው ላይ የስድብ ቃል ሳይሰነዝሩ ይዛችሁ እዚህ ድረስ እንዲያው አምጥታችኋቸዋል።

38. እንግዲህ፣ ድሜጥሮስና ከእርሱ ጋር ያሉት አንጥረኞች በማንም ላይ አቤቱታ ካላቸው፣ ፍርድ ቤቱ ክፍት ነው፤ ዳኞችም አሉ፤ ክስ ማቅረብ ይችላሉ።

39. ከዚህ ሌላ ልታቀርቡ የፈለጋችሁት ነገር ካለ፣ በሕጋዊ ጉባኤ ይታያል።

40. አለበለዚያ ዛሬ ስለ ሆነው ነገር፣ በሁከት አነሣሽነት እንዳንከሰስ ያሠጋናል፤ አጥጋቢ ምክንያት ስለሌለንም፣ ስለ ሁከቱ ብንጠየቅበት መልስ መስጠት አንችልም።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 19