ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 15:3-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. ቤተ ክርስቲያኒቱም እግረ መንገዳቸውን በፊንቄና በሰማርያ በኩል እንዲያልፉ ላከቻቸው፤ እነርሱም በእነዚህ ቦታዎች ለነበሩት የአሕዛብን መመለስና ማመን ነገሯቸው፤ ወንድሞችም ሁሉ በዚህ እጅግ ደስ አላቸው።

4. ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜም፣ ቤተ ክርስቲያንና ሐዋርያት እንዲሁም ሽማግሌዎች ተቀበሏቸው፤ የተላኩትም እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ሆኖ የሠራውን ሁሉ ነገሯቸው።

5. ከፈሪሳውያን ወገን ያመኑት አንዳንዶቹ ተነሥተው በመቆም፣ “አሕዛብ እንዲገረዙና የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ማድረግ አስፈላጊ ነው” አሉ።

6. ሐዋርያትና ሽማግሌዎችም ይህንኑ ጒዳይ ለማጤን ተሰበሰቡ።

7. ከብዙ ክርክር በኋላ ጴጥሮስ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ወንድሞች ሆይ፤ እግዚአብሔር ከጥቂት ጊዜ በፊት በእናንተ መካከል እኔን መርጦ፣ አሕዛብ የወንጌልን ቃል ከእኔ አንደበት ሰምተው እንዲያምኑ ማድረጉን ታውቃላችሁ።

8. ልብን የሚያውቅ አምላክ ለእኛ እንደ ሰጠን ሁሉ፣ ለእነርሱም መንፈስ ቅዱስን በመስጠት የተቀበላቸው መሆኑን መሰከረላቸው፤

9. ልባቸውንም በእምነት በማንጻት በእኛና በእነርሱ መካከል ምንም ልዩነት አላደረገም።

10. እንግዲህ፣ አባቶቻችንም እኛም ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በደቀ መዛሙርት ጫንቃ ላይ በመጫን ለምን አሁን እግዚአብሔርን ትፈታተኑታላችሁ?

11. እኛም የዳንነው ልክ እንደ እነርሱ በጌታ በኢየሱስ ጸጋ መሆኑን እናምናለን።”

12. ጉባኤውም በሙሉ ዝም ብሎ፣ በርናባስና ጳውሎስ እግዚአብሔር በእነርሱ አማካይነት በአሕዛብ መካከል ስላደረጋቸው ታምራዊ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች ሲናገሩ ያዳምጣቸው ነበር።

13. እነርሱም ተናግረው ሲጨርሱ፣ ያዕቆብ ተነሥቶ በመቆም እንዲህ አለ፤ “ወንድሞች ሆይ፤ ስሙኝ፤

14. እግዚአብሔር ከአሕዛብ ወገን ለእርሱ የሚሆነውን ሕዝብ አስቀድሞ እንዴት እንደ ጐበኘ ስምዖን አስረድቶናል።

15. እንዲህ ተብሎ የተጻፈው የነቢያቱም ቃል ከዚህ ጋር ይስማማል፤

16. “ ‘ከዚህ በኋላ እመለሳለሁ፤የፈረሰውን የዳዊትን ቤት እገነባለሁ።ፍርስራሹን መልሼ አቆማለሁ፤እንደ ገናም እሠራዋለሁ፤

17. ይኸውም የቀሩት ሰዎች ጌታን እንዲፈልጉ፣ስሜን የተሸከሙ አሕዛብም እንዲሹኝ ነው፤እነዚህን ያደረገ ጌታ እንዲህ ይላል፤’

18. እነርሱም ከጥንት ጀምሮ የታወቁ ናቸው።

19. “ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር የተመለሱትን አሕዛብ እንዳናስጨንቃቸው ይህ የእኔ ብያኔ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 15