ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 14:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በኢቆንዮንም ጳውሎስና በርናባስ አብረው ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ፤ በዚያም በሚገባ ስላስተማሩ፣ ከአይሁድም ከግሪክም እጅግ ብዙ ሰዎች አመኑ።

2. ያላመኑት አይሁድ ግን፣ አሕዛብን አነሣሥተው ወንድሞችን እንዲጠሉ አደረጓቸው።

3. ጳውሎስና በርናባስም ስለ ጌታ በድፍረት እየተናገሩ ብዙ ጊዜ እዚያው ቈዩ፤ ጌታም የሚናገሩትን የጸጋውን ቃል በታምራዊ ምልክትና በድንቅ ሥራ እየደገፈ ያረጋግ ጥላቸው ነበር።

4. የከተማውም ሕዝብ ተከፋፈለ፤ ገሚሱ ከአይሁድ ጋር፣ ገሚሱም ከሐዋርያት ጋር ሆነ።

5. በዚህ ጊዜ አሕዛብና አይሁድ ከመሪዎቻቸው ጋር ተባብረው ሊያንገላቷቸውና በድንጋይ ሊያስወግሯቸው ሞከሩ።

6. እነርሱ ግን ይህን እንዳወቁ ልስጥራንና ደርቤን ወደተባሉት ወደ ሊቃኦንያ ከተሞችና በዙሪያቸው ወዳለው አገር ሸሹ፤

7. በዚያም ወንጌልን መስበክ ቀጠሉ።

8. በልስጥራንም፣ እግሩ አንካሳ የሆነና ከተወለደ ጀምሮ ፈጽሞ በእግሩ ሄዶ የማያውቅ ሽባ ሰው ተቀምጦ ነበር።

9. ይህም ሰው ጳውሎስ ሲናገር ያደምጥ ነበር። ጳውሎስም ወደ እርሱ ትኵር ብሎ ተመለከተና ለመዳን እምነት እንዳለው ባየ ጊዜ

10. በታላቅ ድምፅ፣ “ቀጥ ብለህ በእግርህ ቁም!” አለው፤ በዚህ ጊዜ ዘሎ ተነሣና መራመድ ጀመረ።

11. ሕዝቡም ጳውሎስ ያደረገውን ባዩ ጊዜ፣ በሊቃኦንያ ቋንቋ፣ “አማልክት በሰው ተመስለው ወደ እኛ ወርደዋል!” ብለው ጮኹ፤

12. በርናባስን ‘ድያ’ አሉት፤ ጳውሎስም ዋና ተናጋሪ ስለ ነበር ‘ሄርሜን’ አሉት።

13. ከከተማው ወጣ ብሎ የነበረው፣ የድያ ቤተ መቅደስ ካህንም ኰርማዎችንና የአበባ ጒንጒኖችን ወደ ከተማው መግቢያ አምጥቶ፣ ከሕዝቡ ጋር ሆኖ ሊሠዋላቸው ፈለገ።

14. ሐዋርያቱ በርናባስና ጳውሎስ ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቡ መካከል ሮጡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 14