ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 13:38-52 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

38. እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ የኀጢአት ይቅርታ የሚገኘው በኢየሱስ በኩል መሆኑ እንደ ተሰበከላችሁ ዕወቁ፤

39. በእርሱ የሚያምን ሁሉ በሙሴ ሕግ በኩል ማግኘት ያልተቻለውን ጽድቅ ያገኛል።

40. ስለዚህ ነቢያት እንዲህ ብለው የተናገሩት እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ፤

41. “ ‘እናንት ፌዘኞች፤ ተመልከቱ፤ተደነቁ፤ ጥፉም፤ማንም ቢነግራችሁ፣የማታምኑትን ሥራ፣እኔ በዘመናችሁ እሠራለሁና።’ ”

42. ጳውሎስና በርናባስ ከምኵራብ ሲወጡ፣ ሰዎቹ ስለ ዚሁ ነገር በሚቀጥለው ሰንበት እንዲነግሯቸው ለመኗቸው።

43. ጉባኤው ከተበተነ በኋላም፣ ብዙ አይሁድና ወደ ይሁዲ ሃይማኖት ገብተው በመንፈሳዊ ነገር የበረቱ ሰዎች፣ ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሏቸው፤ እነርሱም አነጋገሯቸው፤ በእግዚአብሔርም ጸጋ ጸንተው እንዲኖሩ መከሯቸው።

44. በሚቀጥለውም ሰንበት የከተማው ሕዝብ፣ ጥቂቱ ሰው ብቻ ሲቀር፣ በሙሉ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ተሰበሰቡ።

45. አይሁድም ብዙ ሕዝብ ባዩ ጊዜ፣ በቅናት ተሞሉ፤ የጳውሎስንም ንግግር እየተቃወሙ ይሰድቡት ነበር።

46. ጳውሎስና በርናባስም በድፍረት እንዲህ አሏቸው፤ “የእግዚአብሔር ቃል በመጀመሪያ ለእናንተ መነገር አለበት፤ እናንተ ግን ናቃችሁት፤ በዚህም የዘላለም ሕይወት እንደማ ይገባችሁ በራሳችሁ ላይ ስለ ፈረዳችሁ፣ እኛም ወደ አሕዛብ ዞር ለማለት እንገደዳለን።

47. ደግሞም ጌታ እንዲህ ብሎ አዞናል፤“ ‘ድነትን እስከ ምድር ዳርቻ ታደርስ ዘንድ፣ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ።’ ”

48. አሕዛብ ይህን በሰሙ ጊዜ ደስ አላቸው፤ ለእግዚአብሔርም ቃል ክብርን ሰጡ፤ ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁትም ሁሉ አመኑ።

49. የጌታም ቃል በአካባቢው ባለው አገር ሁሉ ተስፋፋ።

50. አይሁድ ግን በመንፈሳዊ ነገር የተጉትንና በኑሮ የከበሩትን ሴቶች እንዲሁም የከተማውን ታላላቅ ወንዶች ቀስቅሰው በጳውሎስና በበርናባስ ላይ ስደትን አስነሡ፤ ከአገራቸውም አስወጧቸው።

51. ጳውሎስና በርናባስም ተቃውሞአቸውን ለመግለጽ የእግራቸውን ትቢያ አራግፈው ወደ ኢቆንዮን ሄዱ።

52. ደቀ መዛሙርቱም በደስታና በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 13