ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 9:20-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. እርሱም፣ “እናንተስ ማን ነው ትሉኛላችሁ?” አላቸው።ጴጥሮስም፣ “አንተ የእግዚአብሔር መሲሕ ነህ” ሲል መለሰለት።

21. ኢየሱስም ይህን ለማንም እንዳይናገሩ አጥብቆ አስጠነቀቃቸው፤

22. ደግሞም፣ “የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበል ይገባዋል፤ እንዲሁም በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሓፍት ዘንድ መናቅ፣ መገደልና በሦስተኛውም ቀን ከሙታን መነሣት አለበት” አላቸው።

23. ከዚያም ለሁሉም እንዲህ አላቸው፤ “በኋላዬ ሊመጣ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም በየዕለቱ ተሸክሞ ይከተለኝ፤

24. ምክንያቱም ነፍሱን ሊያድናት የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፤ ነፍሱን ስለ እኔ ብሎ የሚያጠፋት ግን ያድናታል።

25. ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ወይም ቢያጐድል ጥቅሙ ምንድን ነው?

26. ማንም በእኔና በቃሌ ቢያፍር፣ የሰው ልጅ በራሱ ክብር እንዲሁም በአብና በቅዱሳን መላእክት ክብር ሲመጣ ያፍርበታል።

27. እውነት እላችኋለሁ፤ እዚህ ከቆሙት መካከል የእግዚአብሔርን መንግሥት ሳያዩ ሞትን የማይቀምሱ ሰዎች አሉ።”

28. ኢየሱስ ይህን ከተናገረ ከስምንት ቀን ያህል በኋላ ጴጥሮስን፣ ዮሐንስንና ያዕቆብን ይዞ ሊጸልይ ወደ አንድ ተራራ ወጣ።

29. በመጸለይ ላይ እንዳለም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም እንደ መብረቅ የሚያንጸባርቅ ነጭ ሆነ።

30. እነሆ፤ ሁለት ሰዎች፣ እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤

31. በክብርም ተገልጠው፣ በኢየሩሳሌም ይፈጸም ዘንድ ስላለው ከዚህ ዓለም ስለ መለየቱ ይናገሩ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 9