ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 8:18-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. እንግዲህ እንዴት እንደምትሰሙ ተጠንቀቁ፤ ላለው ይጨመርለታልና፤ ከሌለው ሁሉ ግን ያው ያለው የሚመስለው እንኳ ይወሰድበታል።”

19. ከዚህ በኋላ የኢየሱስ እናትና ወንድሞቹ እርሱ ወዳለበት መጡ፤ እነርሱም ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ወደ እርሱ ሊቀርቡ አልቻሉም።

20. በዚህ ጊዜ፣ “እናትህና ወንድሞችህ ሊያዩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል” የሚል ወሬ ደረሰው።

21. እርሱም መልሶ፣ “እናቴና ወንድሞቼስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚያደርጉት ናቸው” አላቸው።

22. ከዕለታት አንድ ቀን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጀልባ ላይ ወጣ፤ ኢየሱስም፤ “ወደ ባሕሩ ማዶ እንሻገር” አላቸው፤ ከዚያም ጒዞ ቀጠሉ።

23. እየተጓዙ ሳሉም ኢየሱስ እንቅልፍ ወስዶት ተኛ፤ በዚህ ጊዜ በባሕሩ ላይ ማዕበል ተነሣ፤ ውሃውም ጀልባዋን ዘልቆ ስለ ገባ፣ አደጋ አፋፍ ላይ ደረሱ።

24. ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው፣ “ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ ማለቃችን እኮ ነው!” እያሉ ቀሰቀሱት።እርሱም ነቅቶ ነፋሱንና፣ የውሃውን መናወጥ ገሠጸ፤ በዚህ ጊዜ ነፋሱም፣ ነውጡም ተወ፤ ጸጥታም ሆነ።

25. እርሱም ደቀ መዛሙርቱን፣ “እምነታችሁ የት አለ?” አላቸው።እነርሱም በፍርሀትና በመደነቅ፣ “ይህ ነፋ ስንና ውሃን የሚያዝ፣ እነርሱም የሚታዘዙለት ለመሆኑ እርሱ ማን ነው?” ተባባሉ።

26. ከዚህ በኋላ ከገሊላ ባሻገር ወዳለው ወደ ጌርጌሴኖን አገር በጀልባ ተሻገሩ።

27. ኢየሱስ ከጀልባዋ ወደ ምድር በወረደ ጊዜ፣ አጋንንት ያደረበት አንድ ሰው ከከተማ ወጥቶ አገኘው፤ ይህ ሰው ለብዙ ጊዜ ልብስ ሳይለብስ፣ በቤትም ሳይኖር የመቃብርን ስፍራ ቤቱ ያደረገ ነበር።

28. ኢየሱስንም ባየው ጊዜ እየጮኸ ፊቱ ተደፋ፤ በታላቅ ድምፅም፣ “የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፤ ከእኔ ጋር ምን ጒዳይ አለህ? እንዳታሠቃየኝ እለምንሃለሁ” አለ።

29. ርኩሱ መንፈስ ይህን ያለው ከሰውየው እንዲወጣ ኢየሱስ አዞት ስለ ነበር ነው። ርኩሱ መንፈስ በየጊዜው ስለሚነሣበት ሰውየው በሰንሰለትና በእግር ብረት እየታሰረ ቢጠበቅም የታሰረበትን ሰንሰለት እየበጣጠሰ ያደረበት ጋኔን ወደ በረሓ ይነዳው ነበር።

30. ኢየሱስም፣ “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው።እርሱም ብዙ አጋንንት ገብተውበት ስለ ነበር፣ “ሌጌዎን” አለው።

31. አጋንንቱም እንጦርጦስ ግቡ ብሎ እንዳያዛቸውም አጥብቀው ለመኑት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 8