ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 8:14-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. በእሾኽ መካከል የወደቀውም ቃሉን የሚሰሙት ናቸው፤ እነዚህም ውለው አድረው በምድራዊ ሕይወት ጭንቀት፣ በባለጠግነትና ተድላ ደስታ ታንቀው በሚገባ አያፈሩም።

15. በመልካም መሬት ላይ የወደቀውም ቃሉን ቅንና በጎ በሆነ ልብ ሰምተው የሚጠብቁ፣ ታግሠውም በመጽናት ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።

16. “መብራትን አብርቶ ጋን ውስጥ ወይም በዐልጋ ሥር የሚያስቀምጥ ማንም የለም፤ ይልቁንም ወደ ቤት የሚገቡ ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጠዋል።

17. የማይገለጥ የተሰወረ፣ የማይታወቅ ወደ ብርሃን የማይወጣ፣ የተደበቀ ነገር የለምና።

18. እንግዲህ እንዴት እንደምትሰሙ ተጠንቀቁ፤ ላለው ይጨመርለታልና፤ ከሌለው ሁሉ ግን ያው ያለው የሚመስለው እንኳ ይወሰድበታል።”

19. ከዚህ በኋላ የኢየሱስ እናትና ወንድሞቹ እርሱ ወዳለበት መጡ፤ እነርሱም ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ወደ እርሱ ሊቀርቡ አልቻሉም።

20. በዚህ ጊዜ፣ “እናትህና ወንድሞችህ ሊያዩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል” የሚል ወሬ ደረሰው።

21. እርሱም መልሶ፣ “እናቴና ወንድሞቼስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚያደርጉት ናቸው” አላቸው።

22. ከዕለታት አንድ ቀን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጀልባ ላይ ወጣ፤ ኢየሱስም፤ “ወደ ባሕሩ ማዶ እንሻገር” አላቸው፤ ከዚያም ጒዞ ቀጠሉ።

23. እየተጓዙ ሳሉም ኢየሱስ እንቅልፍ ወስዶት ተኛ፤ በዚህ ጊዜ በባሕሩ ላይ ማዕበል ተነሣ፤ ውሃውም ጀልባዋን ዘልቆ ስለ ገባ፣ አደጋ አፋፍ ላይ ደረሱ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 8