ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 7:21-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. በዚያኑ ጊዜ ኢየሱስ ብዙ ሰዎችን ከበሽታ፣ ከደዌና ከርኩሳን መናፍስት ፈወሳቸው፤ የብዙ ዐይነ ስውራንንም ዐይን አበራ።

22. ከዮሐንስ ተልከው የመጡትንም እንዲህ አላቸው፤ “ሄዳችሁ ያያችሁትንና የሰማችሁትን ለዮሐንስ ንገሩት፤ ዐይነ ስውራን ያያሉ፤ ዐንካሶች በትክክል ይራመዳሉ፤ ለምጻሞች ነጽተዋል፤ ደንቈሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ተነሥተዋል፤ ለድኾችም ወንጌል ይሰበካል፤

23. በእኔ የማይሰናከል ሰው ሁሉ የተባረከ ነው።”

24. የዮሐንስ መልእክተኞች ከሄዱ በኋላ፣ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ይናገር ጀመር፤ እንዲህም አለ፤ “ወደ በረሓ የወጣችሁት ምን ልታዩ ነው? ነፋስ የሚያወዛውዘውን ሸምበቆ?

25. እኮ! ምን ልታዩ ወጣችሁ? ያማረ ልብስ የለበሰውን ሰው ነውን? ባማረ ልብስ የሚሽሞነሞኑና በድሎት የሚኖሩ በቤተ መንግሥት አሉላችሁ።

26. እኮ! ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን ለማየት ይሆን? አዎን፣ እላችኋለሁ፤ ለማየት የወጣችሁት ከነቢይም የሚበልጠውን ነው።

27. እንዲህ ተብሎ የተጻፈለትም እርሱ ነው፤ “ ‘መንገድህን በፊትህ የሚያስተካክል፣ መልእክተኛዬን ከአንተ አስቀድሜ እልካለሁ።’

28. እላችኋለሁ፤ ከሴት ከተወለዱት መካከል ከዮሐንስ የሚበልጥ የለም፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል።”

29. ቀረጥ ሰብሳቢዎች እንኳ ሳይቀሩ፣ ይህን የሰሙ ሁሉ፣ የዮሐንስን ጥምቀት በመጠመቅ ለእግዚአብሔር ተገቢውን ክብር ሰጡት፤

30. ፈሪሳውያንና ሕግ ዐዋቂዎች ግን በዮሐንስ እጅ ባለ መጠመቃቸው፣ እግዚአብሔር ለእነርሱ ያለውን ዐላማ አቃለሉ።

31. ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ የዚህን ትውልድ ሰዎች በምን ልመስላቸው? ምንስ ይመስላሉ?

32. በገበያ ቦታ ተቀምጠው እርስ በርሳቸው እየተጠራሩ እንዲህ የሚባባሉ ልጆችን ይመስላሉ፤ “ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤ አልጨፈራችሁም፤ ሙሾ አወረድንላችሁ፤ አላለቀሳችሁም።’

33. ምክንያቱም መጥምቁ ዮሐንስ እህል ሳይ በላና የወይን ጠጅ ሳይጠጣ ቢመጣ፣ ጋኔን አለበት አላችሁት፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 7