ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 6:35-48 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

35. ነገር ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካም አድርጉ፤ መልሳችሁ ለመቀበል ተስፋ ሳታደርጉም አበድሩ፤ በዚህም ወሮታችሁ ታላቅ ይሆናል፤ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፤ እርሱ ለማያመሰግኑና ለክፉዎች ቸር ነውና።

36. አባታችሁ ርኅሩኅ እንደሆነ እናንተም ርኅሩኆች ሁኑ።

37. “አትፍረዱ፤ አይፈረድባችሁም፤ አትኰንኑ፤ አትኰነኑም። ይቅር በሉ፤ ይቅር ትባላላችሁ።

38. ስጡ፤ ይሰጣችኋል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ስለሚሰፈርላችሁ፣ ጫን በተደረገ፣ በተነቀነቀና በተትረፈረፈ መልካም መስፈሪያ ተሰፍሮ በዕቅፋችሁ ይሰጣችኋል።”

39. ደግሞም ይህን ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን? ሁለቱ ተያይዘው ጒድጓድ አይገቡምን?

40. ደቀ መዝሙር ከመምህሩ አይበልጥም፤ ነገር ግን በሚገባ የተማረ ሰው ሁሉ እንደ መምህሩ ይሆናል።

41. “በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጒድፍ ለምን ታያለህ? በራስህ ዐይን ውስጥ የተጋደመውን ግንድ አትመለከትምን?

42. በራስህ ዐይን ውስጥ ያለውን ግንድ ሳታይ ወንድምህን፣ ‘ወንድሜ ሆይ፤ በዐይንህ ውስጥ ያለውን ጒድፍ ላውጣልህ’ እንዴት ልትለው ትችላለህ? አንተ ግብዝ፤ በመጀመሪያ በዐይንህ ውስጥ የተጋደመውን ግንድ አውጣ፤ ከዚያ በኋላ በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጒድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ።

43. “መልካም ዛፍ ሆኖ ሳለ መጥፎ ፍሬ የሚያፈራ የለም፤ እንዲሁም መጥፎ ዛፍ ሆኖ መልካም ፍሬ የሚያፈራ የለም።

44. ዛፍ ሁሉ በፍሬው ይታወቃል፤ ከእሾኽ የበለስ ፍሬ አይለቀምም፤ ከቀጋ ቁጥቋጦ የወይን ፍሬ አይቈረጥም።

45. መልካም ሰው በልቡ ከሞላው መልካም ነገር መልካሙን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም በልቡ ከሞላው ክፉ ነገር ክፉውን ያወጣል፤ ሰው በልቡ ሞልቶ የተረፈውን በአፉ ይናገራልና።

46. “እኔ የምለውን አታደርጉም፤ ታዲያ ለምን፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ’ ትሉኛላችሁ?

47. ወደ እኔ የሚመጣ፣ ቃሌንም ሰምቶ የሚፈጽም ሁሉ ማንን እንደሚመስል ላሳያችሁ፤

48. ቤት ለመሥራት አጥልቆ የቈፈረና በዐለት ላይ መሠረቱን የመሠረተ ሰው ይመስላል፤ ጐርፍ በመጣ ጊዜ የውሃው ሙላት ያን ቤት ገፋው፤ በሚገባ ስለ ታነጸም ሊያነቃንቀው አልቻለም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 6