ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 6:32-43 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

32. “የሚወዷችሁን ብትወዱ ምን የተለየ ዋጋ ታገኛላችሁ? ኀጢአተኞችም እንኳ የሚወዷቸውን ይወዳሉና።

33. መልካም ላደረጉላችሁ መልካም ብታደርጉ ምን የተለየ ዋጋ ታገኛላችሁ? ኀጢአተኞችም እንኳ እንደዚያ ያደርጋሉና።

34. ብድር ይመልሳሉ ለምትሉት ብታበድሩ ምን የተለየ ዋጋ ታገኛላችሁ? ኀጢአተኞችም እንኳ ያበደሩትን ያህል መልሰው ለመቀበል ‘ለኀጢአተኞች’ ያበድራሉ።

35. ነገር ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካም አድርጉ፤ መልሳችሁ ለመቀበል ተስፋ ሳታደርጉም አበድሩ፤ በዚህም ወሮታችሁ ታላቅ ይሆናል፤ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፤ እርሱ ለማያመሰግኑና ለክፉዎች ቸር ነውና።

36. አባታችሁ ርኅሩኅ እንደሆነ እናንተም ርኅሩኆች ሁኑ።

37. “አትፍረዱ፤ አይፈረድባችሁም፤ አትኰንኑ፤ አትኰነኑም። ይቅር በሉ፤ ይቅር ትባላላችሁ።

38. ስጡ፤ ይሰጣችኋል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ስለሚሰፈርላችሁ፣ ጫን በተደረገ፣ በተነቀነቀና በተትረፈረፈ መልካም መስፈሪያ ተሰፍሮ በዕቅፋችሁ ይሰጣችኋል።”

39. ደግሞም ይህን ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን? ሁለቱ ተያይዘው ጒድጓድ አይገቡምን?

40. ደቀ መዝሙር ከመምህሩ አይበልጥም፤ ነገር ግን በሚገባ የተማረ ሰው ሁሉ እንደ መምህሩ ይሆናል።

41. “በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጒድፍ ለምን ታያለህ? በራስህ ዐይን ውስጥ የተጋደመውን ግንድ አትመለከትምን?

42. በራስህ ዐይን ውስጥ ያለውን ግንድ ሳታይ ወንድምህን፣ ‘ወንድሜ ሆይ፤ በዐይንህ ውስጥ ያለውን ጒድፍ ላውጣልህ’ እንዴት ልትለው ትችላለህ? አንተ ግብዝ፤ በመጀመሪያ በዐይንህ ውስጥ የተጋደመውን ግንድ አውጣ፤ ከዚያ በኋላ በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጒድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ።

43. “መልካም ዛፍ ሆኖ ሳለ መጥፎ ፍሬ የሚያፈራ የለም፤ እንዲሁም መጥፎ ዛፍ ሆኖ መልካም ፍሬ የሚያፈራ የለም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 6