ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 5:23-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

23. ‘ኀጢአትህ ተሰረየችልህ’ ከማለትና ‘ተነሥተህ ሂድ’ ከማለት የትኛው ይቀላል?

24. ነገር ግን ይህን ያልሁት የሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን ለማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው ታውቁ ዘንድ ነው።” ከዚያም ሽባውን ሰው፣ “ተነሥተህ ዐልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ እልሃለሁ” አለው።

25. እርሱም ወዲያው ተነሥቶ በፊታቸው ቆመ፤ ተኝቶበት የነበረውንም ተሸክሞ፣ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ ቤቱ ሄደ።

26. በዚህ ጊዜ ሁሉንም መገረም ያዛቸው፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፣ “ዛሬኮ ድንቅ ነገር አየን” እያሉ በፍርሀት ተዋጡ።

27. ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ሄደ፤ ሌዊ የተባለ አንድ ቀረጥ ሰብሳቢም በቀረጥ መቀበያው ቦታ ተቀምጦ አየውና፣ “ተከተለኝ” አለው፤

28. እርሱም ሁሉን ትቶ ተነሥቶ ተከተለው።

29. ሌዊም ለኢየሱስ በቤቱ ትልቅ ግብዣ አደረገ፤ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ሌሎች ሰዎችም ከእነርሱ ጋር በማእድ ተቀምጠው ነበር።

30. ፈሪሳውያንና ጸሐፍታቸውም “ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ‘ከኀጢአተኞች’ ጋር የምትበሉትና የምትጠጡት ለምንድን ነው?” እያሉ በደቀ መዛሙርቱ ላይ አጒረመረሙ።

31. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “በሽተኞች እንጂ ጤነኞች ሐኪም አያስፈልጋቸውም፤

32. እኔም ኀጢአተኞችን ወደ ንስሓ ልመልስ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም።”

33. እነርሱም፣ “የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት አብዛኛውን ጊዜ ይጾማሉ፤ ይጸልያሉ፤ የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርትም እንደዚሁ ያደርጋሉ፤ የአንተዎቹ ግን ዘወትር ይበላሉ፤ ይጠጣሉ” አሉት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 5