ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 5:20-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ፣ “አንተ ሰው፤ ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል” አለው።

21. ጸሐፍትና ፈሪሳውያንም፣ “ይህ አምላክን በመዳፈር እንዲህ የሚናገር ማን ነው? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ኀጢአትን ሊያስተስረይ ማን ይችላል?” ብለው ያስቡ ጀመር።

22. ኢየሱስም ሐሳባቸውን ስለ ተረዳ እንዲህ አላቸው፤ “ለምን በልባችሁ እንዲህ ታስባላችሁ?

23. ‘ኀጢአትህ ተሰረየችልህ’ ከማለትና ‘ተነሥተህ ሂድ’ ከማለት የትኛው ይቀላል?

24. ነገር ግን ይህን ያልሁት የሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን ለማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው ታውቁ ዘንድ ነው።” ከዚያም ሽባውን ሰው፣ “ተነሥተህ ዐልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ እልሃለሁ” አለው።

25. እርሱም ወዲያው ተነሥቶ በፊታቸው ቆመ፤ ተኝቶበት የነበረውንም ተሸክሞ፣ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ ቤቱ ሄደ።

26. በዚህ ጊዜ ሁሉንም መገረም ያዛቸው፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፣ “ዛሬኮ ድንቅ ነገር አየን” እያሉ በፍርሀት ተዋጡ።

27. ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ሄደ፤ ሌዊ የተባለ አንድ ቀረጥ ሰብሳቢም በቀረጥ መቀበያው ቦታ ተቀምጦ አየውና፣ “ተከተለኝ” አለው፤

28. እርሱም ሁሉን ትቶ ተነሥቶ ተከተለው።

29. ሌዊም ለኢየሱስ በቤቱ ትልቅ ግብዣ አደረገ፤ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ሌሎች ሰዎችም ከእነርሱ ጋር በማእድ ተቀምጠው ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 5