ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 4:17-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. የነቢዩ ኢሳይያስ ጥቅልል መጽሐፍም ተሰጠው፤ ጥቅልሉንም መጽሐፍ በተረተረው ጊዜ እንዲህ ተብሎ የተጻፈበትን ክፍል አገኘ፤

18. “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እርሱ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩት መፈታትን፣ ለታወሩትም ማየትን እንዳውጅ፣ የተጨቈኑትን ነጻ እንዳወጣ፣

19. የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እንዳውጅ ልኮኛል።”

20. ከዚያም መጽሐፉን ጠቅልሎ ለአገልጋዩ መልሶ ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኵራብ የነበሩትም ሁሉ ትኵር ብለው ይመለከቱት ነበር።

21. እርሱም፣ “ይህ በጆሮአችሁ የሰማችሁት የመጽሐፍ ቃል ዛሬ ተፈጸመ” ይላቸው ጀመር።

22. ሁሉም ስለ እርሱ በበጎ ይናገሩ ነበር፤ ደግሞም ከአንደበቱ በሚወጣ የጸጋ ቃል እየተገረሙ፣ “ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን?” ይሉ ነበር።

23. እርሱም፣ “ ‘ባለ መድኀኒት ሆይ፤ ራስህን ፈውስ፤ በቅፍርናሆም ስታደርግ የሰማነውን ነገር እዚህ በራስህ ከተማ ደግሞ አድርግ’ የሚለውን ምሳሌ እንደምትጠቅሱብኝ ጥርጥር የለውም” አላቸው።

24. ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ነቢይ በገዛ አገሩ አይከበርም።

25. ነገር ግን እውነት እላችኋለሁ፤ ሰማይ ሦስት ዓመት ከመንፈቅ ተዘግቶ ጽኑ ራብ በምድሪቱ ሁሉ ላይ በነበረበት በኤልያስ ዘመን፣ ብዙ መበለቶች በእስራኤል ነበሩ፤

26. ኤልያስ ከእነዚህ መካከል ወደ አንዷም አልተላከም፤ ነገር ግን በሲዶና አገር በሰራፕታ ወደ ነበረችው መበለት ተላከ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 4