ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 3:8-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. እንግዲህ ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አፍሩ፤ ደግሞም በልባችሁ፣ ‘አብርሃም አባታችን አለን’ ማለትን አትጀምሩ፤ እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ማስነሣት እንደሚችል እነግራችኋለሁና።

9. አሁን እንኳ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ መልካም ፍሬ የማያፈራም ዛፍ ሁሉ ተቈርጦ ወደ እሳት ይጣላል።”

10. ሕዝቡም፣ “ታዲያ፣ ምን እናድርግ?” ብለው ጠየቁት።

11. ዮሐንስም፣ “ሁለት ልብስ ያለው ምንም ለሌለው ያካፍል፤ ምግብ ያለውም እንዲሁ ያድርግ” ብሎ መለሰላቸው።

12. ቀረጥ ሰብሳቢዎችም ሊጠመቁ ወደ እርሱ መጥተው፣ “መምህር ሆይ፤ እኛስ ምን እናድርግ?” አሉት።

13. እርሱም፣ “ከታዘዛችሁት በላይ ቀረጥ አትሰብስቡ” አላቸው።

14. ወታደሮች ደግሞ፣ “እኛስ ምን እናድርግ?” ብለው ጠየቁት።እርሱም፣ “የማንንም ገንዘብ በግፍ አትንጠቁ፤ ሰውንም በሐሰት አትክሰሱ፤ ደመወዛችሁ ይብቃችሁ” አላቸው።

15. ሕዝቡ በጒጒት እየተጠባበቁ ሳሉ፣ “እርሱ ክርስቶስ ይሆንን?” እያሉ ሁሉም በልባቸው ስለ ዮሐንስ ያሰላስሉ ነበር።

16. ዮሐንስ ለሁሉም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ እኔም የእርሱን የጫማ ማሰሪያ መፍታት የሚገባኝ አይደለሁም፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤

17. ዐውድማውን ፈጽሞ ለማጥራትና ስንዴውንም ወደ ጐተራው ለመክተት መንሹ በእጁ ነው፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 3