ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 24:31-45 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

31. በዚህ ጊዜ ዐይናቸው ተከፈተ፤ ዐወቁትም፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ።

32. እነርሱም፣ “በመንገድ ሳለን፣ እያነጋገረን ቅዱሳት መጻሕፍትንም ገልጦ ሲያስረዳን፣ ልባችን እንደ እሳት ይቃጠልብን አልነበረምን?” ተባባሉ።

33. በዚያኑም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዐሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም በዚያ በአንድነት ተሰብስበው አገኟቸው፤

34. “እነርሱም ጌታ በእርግጥ ተነሥቶአል! ለስምዖንም ታይቶአል” ይባባሉ ነበር።

35. ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም በመንገድ ላይ የሆነውንና ኢየሱስ እንጀራውን በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንዳወቁት ተረኩላቸው።

36. ይህን እየተነጋገሩ ሳሉ፣ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው።

37. እነርሱ ግን ደንግጠው በፍርሀት ተዋጡ፤ መንፈስም ያዩ መሰላቸው።

38. እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ለምን ትጨነቃላችሁ? ለምንስ ጥርጣሬ በልባችሁ ይገባል?

39. እጆቼንና እግሮቼን ተመልከቱ፤ እኔው ራሴ ነኝ። ደግሞም ንኩኝና እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት መንፈስ ሥጋና ዐጥንት የለውምና።”

40. ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው።

41. እነርሱም ከመደሰትና ከመገረም የተነሣ ገና ሳያምኑ፣ “በዚያ ቦታ አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?” አላቸው።

42. እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራሽ ሰጡት፤

43. እርሱም ተቀብሎ በፊታቸው በላ።

44. እርሱም፣ “ከእናንተ ጋር በነበርሁበት ጊዜ፣ ‘በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙር መጻሕፍት ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል’ ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው” አላቸው።

45. በዚህ ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲያስተውሉ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 24