ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 23:34-43 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

34. ኢየሱስም፣ “አባት ሆይ፤ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” አለ። እነርሱም ልብሱን በዕጣ ተከፋፈሉት።

35. ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር። ገዦችም፣ “ሌሎችን አዳነ፤ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ እርሱ ከሆነ፣ እስቲ ራሱን ያድን” እያሉ አፌዙበት።

36. ወታደሮችም ቀርበው ያፌዙበት ነበር፤ የሖመጠጠ የወይን ጠጅ እየሰጡትም፣

37. “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ከሆንህ፣ ራስህን አድን” ይሉት ነበር።

38. ከራሱም በላይ፣ “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው” የሚል ጽሑፍ ነበር።

39. ከተሰቀሉት ወንጀለኞችም አንዱ የስድብ ናዳ እያወረደበት፣ “አንተ ክርስቶስ አይደለህምን? እስቲ፣ ራስህንም እኛንም፣ አድን” ይለው ነበር።

40. ሌላኛው ወንጀለኛ ግን እንዲህ ሲል ገሠጸው፤ “ተመሳሳይ ፍርድ እየተቀበልህ ሳለህ፣ ከቶ እግዚአብሔርን አትፈራምን?

41. እኛ ላደረግነው ነገር ቅጣት እየተቀበልን ስለ ሆነ፣ ተገቢ ፍርድ ላይ ነን፤ ይህ ሰው ግን አንዳች ክፉ ነገር አላደረገም።”

42. ደግሞም፣ “ኢየሱስ ሆይ፤ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” አለው።

43. ኢየሱስም፣ “እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 23