ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 23:21-35 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. እነርሱ ግን፣ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ይጮኹ ነበር።

22. ጲላጦስም ሦስተኛ ጊዜ፣ “ለምን? ይህ ሰው ምን የፈጸመው ወንጀል አለ? እኔ ለሞት የሚያበቃ ምንም በደል አላገኘሁበትም፤ ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ” አላቸው።

23. እነርሱ ግን ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እንዲሰቀል አጥብቀው ለመኑት፤ ጩኸታቸውም በረታ።

24. ስለዚህ ጲላጦስ የጠየቁት እንዲፈጸም ውሳኔ አስተላለፈ።

25. የሕዝብ ዐመፅ በማነሣሣትና በነፍስ ግድያ ታስሮ የነበረውን፣ እንዲፈታላቸውም የለመኑትን ያን ሰው ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን እንዳሻቸው እንዲያደርጉት አሳልፎ ሰጣቸው።

26. ኢየሱስንም ይዘው ሲወስዱት፣ ስምዖን የተባለውን የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ አግኝተው መስቀሉን አሸክመው ኢየሱስን ተከትሎ እንዲሄድ አስገደዱት።

27. ብዙ ሕዝብና ደረታቸውን እየደቁ የሚያለቅሱለት ሴቶችም ከኋላው ይከተሉት ነበር።

28. ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አላቸው፤ “እናንት የኢየሩሳሌም ሴቶች፤ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ለእኔ አታልቅሱ፤

29. እነሆ፤ ‘መካኖችና ያልወለዱ ማሕፀኖች፣ ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው’ የምትሉበት ጊዜ ይመጣልና።

30. በዚያን ጊዜም፣ “ ‘ተራሮችን፣ “ውደቁብን” ኰረብቶችንም፣ “ሰውሩን” ይላሉ።’

31. እንግዲህ በእርጥብ ዕንጨት እንዲህ ካደረጉ፣ በደረቁ ምን ያደርጉ ይሆን?”

32. ከእርሱ ጋር እንዲገደሉ ሌሎች ሁለት ወንጀለኞችን ወሰዷቸው።

33. ቀራንዮ የተባለ ቦታ በደረሱ ጊዜ ሰቀሉት፤ ወንጀለኞቹንም አንዱን በቀኙ፣ ሌላውን በግራው ሰቀሏቸው።

34. ኢየሱስም፣ “አባት ሆይ፤ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” አለ። እነርሱም ልብሱን በዕጣ ተከፋፈሉት።

35. ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር። ገዦችም፣ “ሌሎችን አዳነ፤ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ እርሱ ከሆነ፣ እስቲ ራሱን ያድን” እያሉ አፌዙበት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 23