ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 20:9-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. ከዚህ በኋላ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ለሕዝቡ ይነግራቸው ጀመር፤ “አንድ ሰው የወይን ተክል ተከለ፤ ለገበሬዎችም አከራየና ወደ ሌላ አገር ሄዶ ብዙ ጊዜ ቈየ።

10. በመከርም ወራት፣ ከወይኑ ፍሬ እንዲልኩለት አገልጋዩን ወደ እነዚህ ገበሬዎች ላከ፤ ገበሬዎቹ ግን አገልጋዩን ደብድበው ባዶ እጁን ሰደዱት።

11. ቀጥሎም ሌላ አገልጋዩን ላከ፤ ገበሬዎቹም እርሱንም ደግሞ ደበደቡት፤ አዋርደውም ባዶ እጁን ሰደዱት።

12. አሁንም ቀጥሎ ሦስተኛ አገልጋዩን ላከ፤ ገበሬዎቹም እርሱንም ደግሞ አቊስለው ወደ ውጭ ጣሉት።

13. “የወይኑ ተክል ባለቤትም፣ ‘እንግዲህ ምን ላድርግ? እስቲ ደግሞ የምወደውን ልጄን እልካለሁ፤ ምናልባት እርሱን ያከብሩት ይሆናል’ አለ።

14. “ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩት ጊዜ፣ ይህ እኮ ወራሹ ነው፣ ‘ኑና እንግደለው፤ በዚህም ርስቱ የእኛ ይሆናል’ እየተባባሉ ተመካከሩ፤

15. ከወይኑም ተክል ቦታ ወደ ውጭ አውጥተው ገደሉት። “እንግዲህ የወይኑ ተክል ባለቤት ምን ያደርጋቸዋል?

16. መጥቶ እነዚያን ገበሬዎች ያጠፋቸዋል፤ የወይኑንም ተክል ቦታ ለሌሎች ይሰጣል።”ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ፣ “እንዲህ ያለውንስ አያምጣው” አሉ።

17. ኢየሱስም ወደ እነርሱ ተመልክቶ እንዲህ አላቸው፤ “ ‘ታዲያ ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ’ ተብሎ የተጻፈው ትርጒሙ ምንድን ነው?

18. በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩም በላዩ የሚወድቅበት ሁሉ ይደቃል።”

19. ጸሐፍትና የካህናት አለቆችም ይህንን ምሳሌ የተናገረው በእነርሱ ላይ መሆኑን ስላወቁ፣ በዚያኑ ሰዓት ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ።

20. ኢየሱስን አሳልፈው ለገዥው ኀይልና ሥልጣን ለመስጠት፣ ከአፉ በሚወጣ ቃል ለማጥመድ ይከታተሉት ነበር፤ ስለዚህም ጻድቃን መስለው የሚቀርቡ ሰላዮችን ላኩበት።

21. ሰላዮቹም እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ ትክክለኛውን ነገር እንደምትናገርና እንደምታስተምር እንዲሁም የእግዚአብሔርን መንገድ በእውነት እንደ ምታስተምርና ለማንም እንደማታደላ እናውቃለን።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 20