ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 20:13-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. “የወይኑ ተክል ባለቤትም፣ ‘እንግዲህ ምን ላድርግ? እስቲ ደግሞ የምወደውን ልጄን እልካለሁ፤ ምናልባት እርሱን ያከብሩት ይሆናል’ አለ።

14. “ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩት ጊዜ፣ ይህ እኮ ወራሹ ነው፣ ‘ኑና እንግደለው፤ በዚህም ርስቱ የእኛ ይሆናል’ እየተባባሉ ተመካከሩ፤

15. ከወይኑም ተክል ቦታ ወደ ውጭ አውጥተው ገደሉት። “እንግዲህ የወይኑ ተክል ባለቤት ምን ያደርጋቸዋል?

16. መጥቶ እነዚያን ገበሬዎች ያጠፋቸዋል፤ የወይኑንም ተክል ቦታ ለሌሎች ይሰጣል።”ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ፣ “እንዲህ ያለውንስ አያምጣው” አሉ።

17. ኢየሱስም ወደ እነርሱ ተመልክቶ እንዲህ አላቸው፤ “ ‘ታዲያ ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ’ ተብሎ የተጻፈው ትርጒሙ ምንድን ነው?

18. በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩም በላዩ የሚወድቅበት ሁሉ ይደቃል።”

19. ጸሐፍትና የካህናት አለቆችም ይህንን ምሳሌ የተናገረው በእነርሱ ላይ መሆኑን ስላወቁ፣ በዚያኑ ሰዓት ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ።

20. ኢየሱስን አሳልፈው ለገዥው ኀይልና ሥልጣን ለመስጠት፣ ከአፉ በሚወጣ ቃል ለማጥመድ ይከታተሉት ነበር፤ ስለዚህም ጻድቃን መስለው የሚቀርቡ ሰላዮችን ላኩበት።

21. ሰላዮቹም እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ ትክክለኛውን ነገር እንደምትናገርና እንደምታስተምር እንዲሁም የእግዚአብሔርን መንገድ በእውነት እንደ ምታስተምርና ለማንም እንደማታደላ እናውቃለን።

22. ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?”

23. እርሱ ግን ተንኰላቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤

24. “እስቲ አንድ ዲናር አሳዩኝ፤ በላዩ ያለው የማን መልክና ጽሕፈት ነው?”

25. እነርሱም፣ “የቄሳር ነው” ብለው መለሱለት።እርሱም፣ “እንግዲያውስ የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው።

26. ስለዚህ በተናገረው ቃል በሕዝቡ ፊት ሊያጠምዱት አልቻሉም፤ በመልሱም ተገርመው ዝም አሉ።

27. ትንሣኤ ሙታን የለም ከሚሉት ሰዱቃውያን አንዳንዶቹ ወደ ኢየሱስ መጥተው ጥያቄ አቀረቡለት፤

28. እንዲህም አሉት፤ “መምህር ሆይ፤ አንድ ሰው ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፣ ወንድሙ መበለቲቱን አግብቶ ልጆች በመውለድ ለወንድሙ ዘር እንዲተካ ሙሴ ጽፎልናል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 20