ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 2:42-52 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

42. ልጁም ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ፣ እንደተለመደው ወደ በዓሉ ወጡ።

43. በዓሉን ከፈጸሙ በኋላ፣ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ፣ ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀረ፤ ወላጆቹ ግን መቅረቱን አላወቁም ነበር።

44. አብሮአቸው ያለ መስሎአቸው፣ የአንድ ቀን መንገድ ተጓዙ፤ በኋላ ግን ከዘመዶቻቸውና ከወዳጆቻቸው ዘንድ ይፈልጉት ጀመር፤

45. ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።

46. ከሦስት ቀንም በኋላ፣ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጣቸውና ጥያቄ ሲያቀርብላቸው በቤተ መቅደስ ውስጥ አገኙት፤

47. የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ይደነቁ ነበር።

48. ወላጆቹም ባዩት ጊዜ ተገረሙ፤ እናቱም፣ “ልጄ ሆይ፤ ለምን እንዲህ አደረግኸን? አባትህና እኔኮ ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር” አለችው።

49. እርሱም፣ “ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መገኘት እንደሚገባኝ አላወቃችሁምን?” አላቸው።

50. እነርሱ ግን የተናገራቸው ነገር አልገባቸውም።

51. ከዚያም አብሮአቸው ወደ ናዝሬት ወረደ፤ ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም ይህን ሁሉ ነገር በልቧ ትጠብቀው ነበር።

52. ኢየሱስም በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት አደገ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 2