ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 18:9-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. ራሳቸውን እንደ ጻድቃን በመቊጠር ለሚመኩና ሌሎቹን በንቀት ዐይን ለሚመለከቱ ሰዎች እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤

10. “ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ፣ አንዱ ፈሪሳዊ፣ ሌላው ቀረጥ ሰብሳቢ ነበሩ።

11. ፈሪሳዊውም ቆሞ ስለ ራሱ እንዲህ ይጸልይ ነበር፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔ እንደ ሌላው ሰው ሁሉ ቀማኛ፣ ዐመፀኛ፣ አመንዝራ፣ ይልቁንም እንደዚህ ቀረጥ ሰብሳቢ ባለመሆኔ አመሰግንሃለሁ፤

12. በሳምንት ሁለት ጊዜ እጾማለሁ፤ ከማገኘውም ሁሉ ዐሥራት አወጣለሁ።”

13. “ቀረጥ ሰብሳቢው ግን በርቀት ቆሞ፣ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ማየት እንኳ አልፈለገም፤ ነገር ግን ደረቱን እየደቃ፣ ‘እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔን ኀጢአተኛውን ማረኝ’ ይል ነበር።

14. “እላችኋለሁ፤ ከፈሪሳዊው ይልቅ ይኸኛው በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ጻድቅ ተቈጥሮ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይላልና፤ ራሱን ዝቅ ዝቅ የሚያደርግ ግን ከፍ ይላል።”

15. ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው ሰዎች ሕፃናትን ወደ እርሱ ያመጡ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም ይህን ባዩ ጊዜ ገሠጿቸው።

16. ኢየሱስ ግን ሕፃናቱን ወደ ራሱ ጠርቶ እንዲህ አለ፤ “ሕፃናት ወደ እኔ እንዲመጡ ፍቀዱላቸው፤ አትከልክሏቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ናትና።

17. እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበል ሁሉ ከቶ አይገባባትም።”

18. ከአይሁድ አለቆች አንዱ፣ “ቸር መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ላድርግ?” ሲል ጠየቀው።

19. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም፤

20. ‘አታመንዝር፣ አትግደል፣ አትስረቅ፣ በሐሰት አትመስክር፣ አባትህንና እናትህን አክብር’ የሚለውን ትእዛዝ ታውቃለህ።”

21. ሰውየውም፣ “እነዚህንማ ከልጅነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ” አለው።

22. ኢየሱስም ይህን በሰማ ጊዜ፣ “እንግዲያውስ አንድ ነገር ይቀርሃል፤ ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለድኾች ስጥ፤ በሰማይ መዝገብ ይኖርሃል፤ ከዚያም መጥተህ ተከተለኝ” አለው።

23. ሰውየው ግን ይህን ሲሰማ፣ ብዙ ሀብት ስለ ነበረው በጣም ዐዘነ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 18