ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 15:3-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. ኢየሱስም እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤

4. “ከእናንተ መካከል አንዱ መቶ በጎች ቢኖሩትና ከእነርሱ አንዱ ቢጠፋበት፣ ዘጠና ዘጠኙን በሜዳ ላይ ጥሎ የጠፋውን እስኪያገኝ ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ማን ነው?

5. ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ተሸክሞ፣

6. ወደ ቤቱ ይመለሳል፤ ወዳጆቹንና ጎረቤቶቹንም በአንድነት ጠርቶ፣ ‘የጠፋውን በጌን አግኝቻለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ’ ይላቸዋል።

7. እላችኋለሁ፤ እንደዚሁም ንስሓ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ፣ ንስሓ በሚገባ በአንድ ኀጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል።

8. “ወይም ዐሥር የብር ሳንቲሞች ያላት ሴት ከዐሥሩ አንዱ ቢጠፋባት፣ እስክታገኘው ድረስ መብራት አብርታ፣ ቤቷን ጠርጋ፣ አጥብቃ የማትፈልግ ሴት ማን ናት?

9. ባገኘችውም ጊዜ ወዳጆቿንና ጐረቤቶቿን፣ በአንድነት ጠርታ፣ ‘የጠፋብኝን የብር ሳንቲም አግኝቻለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ’ ትላቸዋለች።

10. እላችኋለሁ፤ እንደዚሁም ንስሓ በሚገባ በአንድ ኀጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል።

11. ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት።

12. ከእነርሱም ታናሹ ልጅ አባቱን፣ ‘አባቴ ሆይ፤ ከሀብትህ ድርሻዬን ስጠኝ’ አለው፤ አባትየውም ሀብቱን ለልጆቹ አካፈላቸው።

13. “ብዙም ቀን ሳይቈይ፣ ታናሹ ልጅ ድርሻውን ሁሉ ጠቅልሎ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፤ በዚያም በማጋጣነት ንብረቱን አባከነ።

14. እርሱም ያለውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ፣ በዚያ አገር ሁሉ ጽኑ ራብ ሆነ፤ ይቸገርም ጀመር።

15. ስለዚህ ከዚያ አገር ነዋሪዎች አንዱን ተጠጋ፤ ሰውየውም ዐሣማ እንዲቀልብለት ወደ ዕርሻው ላከው።

16. ዐሣማዎቹ የሚመገቡትን ዐሠር እንኳ ለመብላት ይመኝ ነበር፤ ነገር ግን ይህን እንኳ የሚሰጠው ሰው አልነበረም።

17. “ልብ በገዛ ጊዜ ግን እንዲህ አለ፤ ‘ስንቱ የአባቴ ሠራተኛ ምግብ ተርፎታል፤ እኔ ግን እዚህ በራብ ልሞት ተቃርቤአለሁ

18. ተነሥቼ ወደ አባቴ ልሂድና፣ እንዲህ ልበለው፤ “አባቴ ሆይ፤ በሰማይና በአንተ ፊት በድያለሁ፤

19. ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም፤ ከተቀጠሩት አገልጋዮችህ እንደ አንዱ ቍጠረኝ።’

20. ስለዚህም ተነሥቶ ወደ አባቱ ሄደ። “ነገር ግን፣ እርሱ ገና ሩቅ ሳለ፣ አባቱ አይቶት ራራለት፤ ወደ እርሱም እየሮጠ ሄዶ ዐቅፎ ሳመው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 15