ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 15:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. አንድ ቀን፣ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና “ኀጢአተኞች” ሁሉ ሊሰሙት በዙሪያው ተሰበሰቡ።

2. ፈሪሳውያንና ጸሐፍትም፣ “ይህ ሰው ኀጢአተኞችን ይቀበላል፤ ከእነርሱም ጋር ይበላል” እያሉ አጒረመረሙ።

3. ኢየሱስም እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤

4. “ከእናንተ መካከል አንዱ መቶ በጎች ቢኖሩትና ከእነርሱ አንዱ ቢጠፋበት፣ ዘጠና ዘጠኙን በሜዳ ላይ ጥሎ የጠፋውን እስኪያገኝ ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ማን ነው?

5. ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ተሸክሞ፣

6. ወደ ቤቱ ይመለሳል፤ ወዳጆቹንና ጎረቤቶቹንም በአንድነት ጠርቶ፣ ‘የጠፋውን በጌን አግኝቻለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ’ ይላቸዋል።

7. እላችኋለሁ፤ እንደዚሁም ንስሓ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ፣ ንስሓ በሚገባ በአንድ ኀጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል።

8. “ወይም ዐሥር የብር ሳንቲሞች ያላት ሴት ከዐሥሩ አንዱ ቢጠፋባት፣ እስክታገኘው ድረስ መብራት አብርታ፣ ቤቷን ጠርጋ፣ አጥብቃ የማትፈልግ ሴት ማን ናት?

9. ባገኘችውም ጊዜ ወዳጆቿንና ጐረቤቶቿን፣ በአንድነት ጠርታ፣ ‘የጠፋብኝን የብር ሳንቲም አግኝቻለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ’ ትላቸዋለች።

10. እላችኋለሁ፤ እንደዚሁም ንስሓ በሚገባ በአንድ ኀጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 15