ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 14:18-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. “ነገር ግን ሁሉም የየራሳቸውን ምክንያት ይፈጥሩ ጀመር፤ አንደኛው፣ ‘ገና አሁን መሬት ስለ ገዛሁ ሄጄ ማየት አለብኝ፤ እባክህ፣ ይቅርታ አድርግልኝ’ አለው።

19. “ሌላኛውም፣ ‘አምስት ጥማድ በሬዎች ገዝቻለሁ፤ እነርሱን ልፈትናቸው ስለ ሆነ እባክህ ይቅርታ አድርግልኝ’ አለ።

20. “ሌላው ደግሞ፣ ‘ገና ሙሽራ ስለ ሆንሁ ልመጣ አልችልም’ አለ።

21. “አገልጋዩም ተመልሶ መጥቶ ይህንኑ ለጌታው ነገረው። በዚህን ጊዜ የቤቱ ጌታ ተቈጥቶ አገልጋዩን፣ ‘ቶሎ ብለህ ወደ ከተማው አውራ ጐዳናዎችና መተላለፊያ መንገዶች ውጣ፤ ድኾችንና አካለ ስንኩሎችን፣ ዐይነ ስውሮችንና ዐንካሶችን ወደዚህ አስገባቸው’ አለው።

22. “አገልጋዩም፣ ‘ጌታዬ፤ ያዘዝኸው ሁሉ ተፈጽሟል፤ ገና አሁንም ቦታ አለ’ አለው።

23. “ጌታውም አገልጋዩን፣ ‘ወደ ጐዳናዎችና ወደ ገጠር መንገዶች ውጣ፤ ቤቴም እንዲሞላ ያገኘኸውን ሁሉ በግድ አምጥተህ አስገባ፤

24. እላችኋለሁና ከተጋበዙት ከእነዚያ ሰዎች መካከል አንድ ሰው እንኳ ግብ ዣዬን አይቀምስም አለው።’ ”

25. ብዙ ሕዝብ አብሮት እየተጓዙ ሳለ፣ ኢየሱስ ዘወር ብሎ እንዲህ አላቸው፤

26. “ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ አባቱንና እናቱን ሚስቱንና ልጆቹን፣ ወንድሞቹንና እኅቶቹን፣ የራሱንም ሕይወት እንኳ ሳይቀር ባይጠላ፣ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም፤

27. የራሱንም መስቀል ተሸክሞ የማይከተለኝ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።

28. “ከእናንተ አንድ ሰው ሕንጻ ለመሥራት ቢፈልግ፣ መደምደም መቻል አለመቻሉን በመጀመሪያ ተቀምጦ ዋጋውን የማይተምን ማን ነው?

29. መሠረቱን ጥሎ መደምደም ቢያቅተው፣ ያዩት ሁሉ ይዘባበቱበታል፤

30. እንዲህም ይላሉ፤ ‘ይህ ሰው ማነጽ ጀምሮ ነበር፤ መደምደም ግን አቃተው።’

31. “ወይም አንድ ንጉሥ ከሌላው ንጉሥ ጋር ጦርነት ሊገጥም በሚነሣበት ጊዜ፣ ሃያ ሺህ ሰራዊት አስከትቶ የሚመጣበትን ንጉሥ፣ በዐሥር ሺህ ሰራዊት መመከት እንደሚችል ተቀምጦ የማይመክር ማን ነው?

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 14