ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 1:2-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. ይህም ታሪክ ከመጀመሪያው አንሥቶ የዐይን ምስክሮችና የቃሉ አገልጋዮች የነበሩት ያስተላለፉልን ነው።

3. ክቡር ቴዎፍሎስ ሆይ፤ እኔም በበኩሌ ሁሉን ከመሠረቱ በጥንቃቄ ከመረመርሁ በኋላ፣ ታሪኩን ቅደም ተከተሉን በጠበቀ ሁኔታ ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ፤

4. ይህንንም የማደርገው የተማርኸው ነገር እውነተኛ መሆኑን እንድታውቅ ነው።

5. በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን፣ ከአብያ የክህነት ምድብ የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱ ኤልሳቤጥም ከአሮን ነገድ ነበረች።

6. ሁለቱም የጌታን ትእዛዝና ሥርዐት ሁሉ ጠብቀው ያለ ነቀፋ የሚኖሩ፣ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤

7. ይሁን እንጂ ኤልሳቤጥ መካን በመሆኗ ልጅ አልነበራቸውም፤ ሁለቱም በዕድሜ የገፉ ነበሩ።

8. አንድ ቀን ዘካርያስ በምድቡ ተራ፣ በእግዚአብሔር ፊት በክህነት በሚያገለግልበት ጊዜ፣

9. በሥርዐተ ክህነቱ መሠረት፣ ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን በዕጣ ተመረጠ።

10. ዕጣን በሚታጠንበትም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ሆኖ ይጸልይ ነበር።

11. የጌታም መልአክ ከዕጣን መሠዊያው በስተ ቀኝ ቆሞ ታየው።

12. ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ በፍርሀትም ተዋጠ።

13. መልአኩ ግን እንዲህ አለው፤ “ዘካርያስ ሆይ፤ አትፍራ፤ ጸሎትህ ተሰምቶአል፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ።

14. በእርሱ ተድላና ደስታ ታገኛለህ፤ ብዙዎችም እርሱ በመወለዱ ደስ ይላቸዋል፤

15. በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና። የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ በእናቱም ማሕፀን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 1