ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ቆሮንቶስ 8:17-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. ምክንያቱም ቲቶ ወደ እናንተ የመጣው ልመናችንን በመቀበል ብቻ ሳይሆን፣ በታላቅ ጒጒትና በራሱ ፈቃድ በመነሣሣት ነበር።

18. ከእርሱም ጋር በወንጌል ስብከት በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የተመሰገነውን ወንድም ልከነዋል።

19. ከዚህም በላይ ስጦታውን በምንወስድበት ጊዜ አብሮን እንዲሄድ በአብያተ ክርስቲያናት ተመርጦአል፤ ስጦታውንም የምንወስደው ጌታን ራሱን ለማክበርና ሌሎችን ለመርዳት ካለን በጎ ፈቃድ የተነሣ ነው።

20. በዚህ በምናከናውነው የቸርነት ሥራ አንዳች ነቀፋ እንዳይገኝብን እንጠነቀቃለን።

21. ምክንያቱም ዐላማችን በጌታ ፊት ብቻ ሳይሆን፣ በሰውም ፊት መልካም የሆነውን ነገር ማድረግ ነው።

22. ደግሞም ብዙ ጊዜ በብዙ መንገድ ተፈትኖ ትጉ ሆኖ የተገኘውን ወንድማችንን ከእነርሱ ጋር ልከነዋል፤ አሁንም በእናንተ እጅግ ከመታመኑ የተነሣ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ እየተጋ ነው።

23. ስለ ቲቶ የሚጠይቅ ቢኖር፣ እርሱ እናንተን ለማገልገል አብሮኝ የሚሠራ ባልደረባዬ ነው፤ ስለ ወንድሞቻችንም የሚጠይቅ ቢኖር እነርሱ የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮችና የክርስቶስ ክብር ናቸው።

24. ስለዚህ የፍቅራችሁን እውነተኛነትና በእናንተም የምንታመነው የቱን ያህል እንደሆነ በአብያተ ክርስቲያናት ፊት ግለጡላቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ቆሮንቶስ 8