ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ቆሮንቶስ 8:13-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. ይህንን የምንለው እናንተ ተቸግራችሁ ሌሎች ይድላቸው ለማለት ሳይሆን፣ ሁላችሁም እኩል እንድትሆኑ ነው።

14. በአሁኑ ጊዜ የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጒድለት ያሟላል፤ የእነርሱም ደግሞ በተራው የእናንተን ጒድለት ያሟላል፤ በዚህም ያላችሁን እኩል ትካፈላላችሁ።

15. ይህም፣ “ብዙ የሰበሰበ አላተረፈም፤ ጥቂት የሰበሰበም አልጐደለበትም” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።

16. እኔ ለእናንተ ያለኝን በጎ ሐሳብ በቲቶ ልብ ውስጥ ያኖረ አምላክ የተመሰገነ ይሁን፤

17. ምክንያቱም ቲቶ ወደ እናንተ የመጣው ልመናችንን በመቀበል ብቻ ሳይሆን፣ በታላቅ ጒጒትና በራሱ ፈቃድ በመነሣሣት ነበር።

18. ከእርሱም ጋር በወንጌል ስብከት በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የተመሰገነውን ወንድም ልከነዋል።

19. ከዚህም በላይ ስጦታውን በምንወስድበት ጊዜ አብሮን እንዲሄድ በአብያተ ክርስቲያናት ተመርጦአል፤ ስጦታውንም የምንወስደው ጌታን ራሱን ለማክበርና ሌሎችን ለመርዳት ካለን በጎ ፈቃድ የተነሣ ነው።

20. በዚህ በምናከናውነው የቸርነት ሥራ አንዳች ነቀፋ እንዳይገኝብን እንጠነቀቃለን።

21. ምክንያቱም ዐላማችን በጌታ ፊት ብቻ ሳይሆን፣ በሰውም ፊት መልካም የሆነውን ነገር ማድረግ ነው።

22. ደግሞም ብዙ ጊዜ በብዙ መንገድ ተፈትኖ ትጉ ሆኖ የተገኘውን ወንድማችንን ከእነርሱ ጋር ልከነዋል፤ አሁንም በእናንተ እጅግ ከመታመኑ የተነሣ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ እየተጋ ነው።

23. ስለ ቲቶ የሚጠይቅ ቢኖር፣ እርሱ እናንተን ለማገልገል አብሮኝ የሚሠራ ባልደረባዬ ነው፤ ስለ ወንድሞቻችንም የሚጠይቅ ቢኖር እነርሱ የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮችና የክርስቶስ ክብር ናቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ቆሮንቶስ 8