ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዮሐንስ 3:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን እንድንጠራ አብ አትረፍርፎ ያፈሰሰልን ፍቅር ምንኛ ታላቅ ነው! እኛም እንዲሁ ልጆቹ ነን። ዓለም እኛን የማያውቀንም እርሱን ስላ ላወቀው ነው።

2. ወዳጆች ሆይ፤ እኛ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፤ ወደ ፊት ምን እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። እርሱ በሚገለጥበት ጊዜ እናየዋለንና፣ እርሱን እንደ ምንመስል እናውቃለን።

3. በእርሱ ይህን ተስፋ የሚያደርግ ሁሉ፣ እርሱ ንጹሕ እንደሆነ ራሱን ያነጻል።

4. ኀጢአት የሚያደርግ ሁሉ ዐመፅን ያደርጋል፤ ኀጢአትም ዐመፅ ነው።

5. እርሱ ኀጢአትን ሊያስወግድ እንደ ተገለጠ ታውቃላችሁ፤ በእርሱም ኀጢአት የለም።

6. በእርሱም የሚኖር ኀጢአትን አያደርግም፤ ኀጢአት የሚያደርግ ግን እርሱን አላየውም ወይም አላወቀውም።

7. ልጆች ሆይ፤ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ እርሱ ጻድቅ እንደሆነ፣ ጽድቅን የሚያደርግ ጻድቅ ነው።

8. ኀጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው። ምክንያቱም ዲያብሎስ ከመጀመሪያ አንሥቶ ኀጢአትን የሚያደርግ ነው። የእግዚአብሔር ልጅ የተገለጠውም የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ ነው።

9. ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኀጢአትን አያደርግም፤ የእርሱ ዘር በውስጡ ይኖራልና፤ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደም ኀጢአትን ሊያደርግ አይችልም።

10. የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች ተለይተው የሚታወቁት በዚህ ነው፦ ጽድቅን የማያደርግ፣ ወንድሙንም የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።

11. ከመጀመሪያ የሰማችኋት፣ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል የምትለዋ መልእክት ይህች ናትና፤

12. የክፉው ወገን ሆኖ ወንድሙን እንደ ገደለው እንደ ቃየን አትሁኑ፤ ለምን ገደለው? ምክንያቱም የእርሱ ሥራ ክፉ፣ የወንድሙ ግን ጽድቅ ስለ ነበረ ነው።

13. ወንድሞች ሆይ፤ ዓለም ቢጠላችሁ አትደነቁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ዮሐንስ 3