ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዮሐንስ 3 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን እንድንጠራ አብ አትረፍርፎ ያፈሰሰልን ፍቅር ምንኛ ታላቅ ነው! እኛም እንዲሁ ልጆቹ ነን። ዓለም እኛን የማያውቀንም እርሱን ስላ ላወቀው ነው።

2. ወዳጆች ሆይ፤ እኛ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፤ ወደ ፊት ምን እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። እርሱ በሚገለጥበት ጊዜ እናየዋለንና፣ እርሱን እንደ ምንመስል እናውቃለን።

3. በእርሱ ይህን ተስፋ የሚያደርግ ሁሉ፣ እርሱ ንጹሕ እንደሆነ ራሱን ያነጻል።

4. ኀጢአት የሚያደርግ ሁሉ ዐመፅን ያደርጋል፤ ኀጢአትም ዐመፅ ነው።

5. እርሱ ኀጢአትን ሊያስወግድ እንደ ተገለጠ ታውቃላችሁ፤ በእርሱም ኀጢአት የለም።

6. በእርሱም የሚኖር ኀጢአትን አያደርግም፤ ኀጢአት የሚያደርግ ግን እርሱን አላየውም ወይም አላወቀውም።

7. ልጆች ሆይ፤ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ እርሱ ጻድቅ እንደሆነ፣ ጽድቅን የሚያደርግ ጻድቅ ነው።

8. ኀጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው። ምክንያቱም ዲያብሎስ ከመጀመሪያ አንሥቶ ኀጢአትን የሚያደርግ ነው። የእግዚአብሔር ልጅ የተገለጠውም የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ ነው።

9. ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኀጢአትን አያደርግም፤ የእርሱ ዘር በውስጡ ይኖራልና፤ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደም ኀጢአትን ሊያደርግ አይችልም።

10. የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች ተለይተው የሚታወቁት በዚህ ነው፦ ጽድቅን የማያደርግ፣ ወንድሙንም የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።

እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ

11. ከመጀመሪያ የሰማችኋት፣ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል የምትለዋ መልእክት ይህች ናትና፤

12. የክፉው ወገን ሆኖ ወንድሙን እንደ ገደለው እንደ ቃየን አትሁኑ፤ ለምን ገደለው? ምክንያቱም የእርሱ ሥራ ክፉ፣ የወንድሙ ግን ጽድቅ ስለ ነበረ ነው።

13. ወንድሞች ሆይ፤ ዓለም ቢጠላችሁ አትደነቁ።

14. ወንድሞቻችንን ስለምንወድ ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ፍቅር የሌለው ሁሉ በሞት ይኖራል።

15. ወንድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳይም የዘላለም ሕይወት እንደሌለው ታውቃላችሁ።

16. ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቱን ስለ እኛ አሳልፎ ስለ ሰጠ፣ ፍቅር ምን እንደሆነ በዚህ እናውቃለን፤ እኛም ሕይወታችንን ስለ ወንድሞቻችን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባናል።

17. ማንም ሀብት እያለው፣ ወንድሙ ሲቸገር አይቶ ባይራራለት፣ የእግዚአብሔር ፍቅር እንዴት በእርሱ ይኖራል?

18. ልጆች ሆይ፤ በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ።

19. እኛ የእውነት ወገን መሆናችንን በዚህ እናውቃለን፤ ልባችንንም በፊቱ እናሳርፋለን፣

20. ይህም ልባችን በእኛ ላይ በሚፈርድብን ነገር ሁሉ ነው። እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉን ነገር ያውቃል።

21. ወዳጆች ሆይ፤ ልባችን የማይፈርድብን ከሆነ በእግዚአብሔር ፊት ድፍረት አለን፤

22. ትእዛዛቱንም ስለምንጠብቅና በፊቱም ደስ የሚያሰኘውን ስለምናደርግ የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እንቀበላለን።

23. ትእዛዙም በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ እንድናምንና እርሱ እንዳዘዘንም እርስ በርሳችን እንድንዋደድ ነው።

24. ትእዛዞቹንም የሚጠብቁ ሁሉ በእርሱ ይኖራሉ፤ እርሱም በእነርሱ ይኖራል። በእኛ መኖሩን በዚህ ይኸውም እርሱ በሰጠን መንፈስ እናውቃለን።