ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ተሰሎንቄ 5 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ወንድሞች ሆይ፤ ስለ ዘመናትና ስለ ወራት ልንጽፍላችሁ አያስፈልግም።

2. ምክንያቱም ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ የጌታም ቀን እንዲሁ እንደሚመጣ እናንተ ራሳችሁ በሚገባ ታውቃላችሁ።

3. ሰዎች፣ “ሰላምና ደኅንነት ነው” ሲሉ፣ ምጥ እርጉዝ ሴትን እንደሚይዛት እንዲሁ ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል፤ ከቶም አያመልጡም።

4. እናንተ ግን፣ ወንድሞች ሆይ፤ ይህ ቀን እንደ ሌባ ያስደነግጣችሁ ዘንድ በጨለማ ውስጥ አይደላችሁም፤

5. ሁላችሁም የብርሃን ልጆች፣ የቀንም ልጆች ናችሁና። እኛ ከሌሊት ወይም ከጨለማ ወገን አይደለንም፤

6. እንግዲህ እንንቃ፤ ራሳችንንም እንግዛ እንጂ እንደሚያንቀላፉት እንደ ሌሎቹ አንሁን።

7. የሚያንቀላፉ በሌሊት ያንቀላፋሉ፤ የሚሰክሩም በሌሊት ይሰክራሉና።

8. እኛ ግን የቀን ሰዎች ስለ ሆንን፣ እምነትንና ፍቅርን እንደ ጥሩር ለብሰን፣ የመዳንን ተስፋ እንደ ራስ ቍር ደፍተን ራሳችንን በመግዛት እንኑር፤

9. እግዚአብሔር ድነትን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንድናገኝ ነው እንጂ ለቍጣ ወስኖ አላስቀመጠንምና።

10. ብንነቃም ሆነ ብናንቀላፋ ከእርሱ ጋር በሕይወት እንድንኖር እርሱ ስለ እኛ ሞተ።

11. ስለዚህ በርግጥ አሁን እንደምታደርጉት ሁሉ እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ፤ አንዱም ሌላውን ያንጽ።

የመጨረሻ ምክር

12. እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ በእናንተ መካከል በትጋት የሚሠሩትን፣ በጌታም የበላዮቻችሁና መካሪዎቻችሁ የሆኑትን እንድታከብሯቸው እንለምናችኋለን፤

13. ስለ ሥራቸውም በፍቅር እጅግ አክብሯቸው። እርስ በርሳችሁም በሰላም ኑሩ።

14. ወንድሞች ሆይ፤ ይህን እንመክራችኋለን፤ ሥራ ፈቶችን ገሥጿቸው፤ ፈሪዎችን አደፋፍሯቸው፤ ደካሞችን እርዷቸው፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ።

15. ማንም በክፉ ፈንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፤ ነገር ግን እርስ በርሳችሁም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ሁል ጊዜ መልካም የሆነውን ነገር ለማድረግ ተጣጣሩ።

16. ሁል ጊዜ ደስ ይበላችሁ፤

17. ሳታቋርጡ ጸልዩ፤

18. በማናቸውም ሁኔታ አመስግኑ፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ለእናንተ ይህ ነውና።

19. የመንፈስን እሳት አታዳፍኑ፤

20. ትንቢትን አትናቁ።

21. ሁሉን ነገር ፈትኑ፤ መልካም የሆነውን ያዙ፤

22. ከማናቸውም ዐይነት ክፉ ነገር ራቁ።

23. የሰላም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁ፣ ነፍሳችሁና ሥጋችሁ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ ያለ ነቀፋ ይጠበቁ።

24. የጠራችሁ የታመነ ነው፤ እርሱም ያደርገዋል።

25. ወንድሞች ሆይ፤ ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ።

26. ወንድሞችን ሁሉ በተቀደሰ አሳሳም ሰላም በሏቸው።

27. ይህ መልእክት ለወንድሞች ሁሉ እንዲነበብ በጌታ ዐደራ እላችኋለሁ።

28. የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።