ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ተሰሎንቄ 4 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ አኗኗር

1. በቀረውስ ወንድሞች ሆይ፤ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት እንዴት መኖር እንደሚገባችሁ አስተምረናችኋል፤ በርግጥም እንደዚያው እየኖራችሁ ነው። ስለ ሆነም በጌታ በኢየሱስ የምንለምናችሁና የምንመክራችሁ ከዚህ በበለጠ ሁኔታ በዚሁ እንድትገፉበት ነው።

2. በጌታ በኢየሱስ ሥልጣን ምን ዐይነት ትእዛዝ እንደ ሰጠናችሁ ታውቃላችሁ።

3. የእግዚአብሔር ፈቃድ ከዝሙት ርቃችሁ እንድትቀደሱ ነው፤

4. ደግሞም እያንዳንዱ የገዛ ሰውነቱን በቅድስናና በክብር መያዝ እንዳለበት እንዲያውቅ ነው፤

5. ይህም እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወተ ሥጋ ምኞት አይሁን።

6. በዚህም ነገር ማንም ተላልፎ ወንድሙን አያታል፤ ምክንያቱም ከዚህ በፊት እንደነገርናችሁና እንዳስጠነቀቅናችሁ ጌታ እንደ እነዚህ ያለውን ኀጢአት ሁሉ የሚፈጽሙትን ይበቀላል፤

7. እግዚአብሔር በቅድስና እንድንመላለስ እንጂ ለርኵሰት አልጠራንምና።

8. እንግዲህ ይህን ምክር ንቆ የማይቀበል፣ የናቀው ቅዱስ መንፈሱን የሰጣችሁን እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አይደለም።

9. ስለ ወንድማማች መዋደድ ማንም እንዲጽፍላችሁ አያስፈልግም፤ ምክንያቱም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ እናንተ ራሳችሁ ከእግዚአብሔር ተምራችኋልና።

10. በመላዪቱ መቄዶንያ የሚገኙትን ወንድሞች ሁሉ እንደምትወዷቸው የታወቀ ነው፤ ነገር ግን ወንድሞች ሆይ፤ ከዚህ በበለጠ እንድትገፉበት እንመክራችኋለን።

11. ከዚህ በፊት እንዳዘዝናችሁ በገዛ እጃችሁ ሥሩ፤ በጸጥታ ኑሩ፤ በራሳችሁ ጒዳይ ላይ ብቻ አተኵሩ።

12. ይውም በዕለት ተለት ኑሮአችሁ በውጭ ባሉት ዘንድ እንዲያስከብራችሁና በማንም ሰው ላይ ሸክም እንዳትሆኑ ነው።

የጌታ ዳግም ምጽአት

13. ወንድሞች ሆይ፤ አንቀላፍተው ስላሉ ሰዎች ሳታውቁ እንድትቀሩ አንፈልግም፤ ደግሞም ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ሰዎች እንድታዝኑ አንሻም።

14. ኢየሱስ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ ካመንን፣ በኢየሱስ ሆነው ያንቀላፉትን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንደዚሁ ያመጣቸዋል።

15. በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህን ነው፤ እኛ በሕይወት ያለንና ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉትን አንቀድምም፤

16. ጌታ ራሱ በታላቅ ትእዛዝ፣ በመላእክት አለቃ ድምፅና በእግዚአብሔር የመለከት ድምፅ ከሰማይ ይወርዳልና። በክርስቶስ የሞቱትም አስቀድመው ይነሣሉ።

17. ከዚያም በኋላ እኛ የቀረነው፣ በሕይወትም የምንኖረው ጌታን በአየር ላይ ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ በዚህም መሠረት ለዘላለም ከጌታ ጋር እንሆናለን።

18. ስለዚህ በዚህ ቃል እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ።