ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ቆሮንቶስ 9:6-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ወይስ ጥረን ግረን መኖር ያለብን እኔና በርናባስ ብቻ ነን?

7. ለመሆኑ በገዛ ገንዘቡ በወታደርነት የሚያገለግል ማን ነው? ወይን ተክሎ ፍሬውን የማይበላ ማን ነው? መንጋ እየጠበቀ የከብቱን ወተት የማይጠጣ ማን ነው?

8. ይህን የምናገረው እንደ ሰው አስተሳሰብ ነውን? የኦሪትስ ሕግ ይህንኑ ይል የለምን?

9. በሙሴ ሕግ፣ “የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር” ተብሎ ተጽፎአልና። ለመሆኑ፣ እግዚአብሔርን ያሳሰበው የበሬ ጒዳይ ነውን?

10. ይህን የተናገረው በርግጥ ስለ እኛ አይደለምን? የተጻፈው በትክክል ስለ እኛ ነው፤ ዐራሹ የሚያርሰው፣ አበራዩ የሚያበራየው ከምርቱ ድርሻ እንዳለው ተስፋ በማድረግ ነውና።

11. እኛ በእናንተ መካከል መንፈሳዊ ዘር ዘርተን ከሆነ ለሥጋ የሚሆን ነገር ብናጭድ ትልቅ ነገር መሆኑ ነውን?

12. ሌሎች ይህን መብት ከእናንተ ማግኘት ከቻሉ፣ እኛ ይበልጥ ማግኘት አይገባንምን?እኛ ግን በዚህ መብት አልተጠቀምንም፤ ይልቁንም ለክርስቶስ ወንጌል ዕንቅፋት እንዳንሆን ሁሉንም ነገር እንታገሣለን።

13. በቤተ መቅደስ የሚያገለግሉ ምግባቸውን ከቤተ መቅደስ እንደሚያገኙ፣ በመሠዊያውም የሚያገለግሉ ከመሥዋዕቱ እንደሚካፈሉ አታውቁምን?

14. እንደዚሁም ወንጌልን የሚሰብኩ ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ከወንጌል እንዲቀበሉ ጌታ አዞአል።

15. እኔ ግን ከእነዚህ መብቶች በአንዱ እንኳ አልተጠቀምሁም፤ አሁንም ይህን የምጽፍላችሁ እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች ታደርጉልኛላችሁ በሚል ተስፋ አይደለም፤ ማንም ትምክሕቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ሞት ይሻለኛልና።

16. ወንጌልን መስበኬ አያስመካኝም፤ የምሰብከው ግዴታዬ ስለ ሆነ ነው፤ ወንጌልን ባልሰብክ ግን ወዮልኝ።

17. በፈቃደኝነት ብሰብክ ሽልማት አለኝ፤ በፈቃደኝነት ካልሆነ ግን፣ የምፈጽመው ተግባር የተጣለብኝን ዐደራ መወጣት ብቻ ይሆናል።

18. ታዲያ ሽልማቴ ምንድን ነው? ሽልማቴማ ወንጌልን ስሰብክ በመብቴ ሳልጠቀም ወንጌልን ያለ ክፍያ መስበክ ነው።

19. እኔ ነጻ ሰው ነኝ፤ የማንም ባሪያ አይደለሁም፤ ነገር ግን ብዙዎችን እመልስ ዘንድ ራሴን ለሰው ሁሉ ባሪያ አደርጋለሁ።

20. አይሁድን እመልስ ዘንድ ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፣ ከሕግ በታች ያሉትን እመልስ ዘንድ ከሕግ በታች እንዳሉት ሆንሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ቆሮንቶስ 9