ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ቆሮንቶስ 15:35-48 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

35. ነገር ግን፣ “ሙታን እንዴት ይነሣሉ? የሚመጡትስ በምን ዐይነት አካል ነው?” የሚል ሰው ሊኖር ይችላል።

36. አንተ ሞኝ! የምትዘራው ካልሞተ ሕይወት አያገኝም።

37. የምትዘራውም የስንዴ ወይም የሌላ ዐይነት ዘር ቅንጣት ብቻ እንጂ ወደ ፊት የምታገኘውን አካል አይደለም።

38. እግዚአብሔር ግን እንደ ፈቀደ አካልን ይሰጠዋል፤ ለእያንዳንዱም የዘር ዐይነት የራሱን አካል ይሰጠዋል።

39. ሥጋ ሁሉ አንድ አይደለም፤ የሰው ሥጋ አንድ ነው፤ የእንስሳት ሥጋ ሌላ ነው፤ የዓሣ ሥጋ ሌላ ዐይነት ነው።

40. እንዲሁም ሰማያውያን አካላት አሉ፤ ምድራውያን አካላት አሉ፤ ነገር ግን የሰማያዊ አካላት ክብር አንድ ነው፤ የምድራዊም አካላት ክብር ሌላ ነው።

41. የፀሓይ ክብር አንድ ዐይነት ነው፤ የጨረቃ ክብር ሌላ ነው፤ የከዋክብት ደግሞ ሌላ ነው፤ የአንዱም ኮከብ ክብር ከሌላው ኮከብ ክብር ይለያል።

42. የሙታን ትንሣኤም እንደዚሁ ነው፤ የሚበሰብስ አካል ይዘራል፤ የማይበሰብስ አካል ሆኖ ይነሣል፤

43. በውርደት ይዘራል፤ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል በኀይል ይነሣል፤

44. ፍጥረታዊ አካል ይዘራል መንፈሳዊ አካል ይነሣል።ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ።

45. ስለዚህ፣ “የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ” ተብሎ ተጽፎአል፤ የኋለኛው አዳም ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ።

46. ነገር ግን በመጀመሪያ የመጣው መንፈሳዊው ሳይሆን ፍጥረታዊው ነው፤ ከዚያም በኋላ መንፈሳዊው መጣ።

47. የመጀመሪያው ሰው ከምድር የተገኘ ምድራዊ ነው፤ የኋለኛው ግን ከሰማይ ነው።

48. ከምድር የሆኑት እንደ ምድራዊው ናቸው፤ ከሰማይ የሆኑትም እንደ ሰማያዊው ናቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ቆሮንቶስ 15