ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ቆሮንቶስ 14:14-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. በልሳን በምጸልይበት ጊዜ መንፈሴ ይጸልያል፤ አእምሮዬ ግን ያለ ፍሬ ነው።

15. ታዲያ፣ ምን ማድረግ አለብኝ? በመንፈስ እጸልያለሁ፤ በአእምሮም ደግሞ እጸልያለሁ፤ በመንፈስ እዘምራለሁ፤ በአእምሮም ደግሞ እዘምራለሁ።

16. እንዲህማ ካልሆነ እግዚአብሔርን በመንፈስ በምታመሰግንበት ጊዜ፣ ለነገሩ እንግዳ የሆነ ሰው አንተ የምትናገረውን ካልተረዳ፣ እንዴት አድርጎ ለምስጋናህ፣ “አሜን” ሊል ይችላል?

17. አንተ በሚገባ ታመሰግን ይሆናል፤ ሌላው ሰው ግን አይታነጽበትም።

18. ከሁላችሁ የበለጠ በልሳን ስለምናገር እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።

19. ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሌሎችን ለማስተማር፣ ዐሥር ሺህ ቃላት በልሳን ከምናገር ይልቅ፣ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ብናገር ይሻላል።

20. ወንድሞች ሆይ፤ በአስተሳሰባችሁ ሕፃናት አትሁኑ፤ ለክፉ ነገር ሕፃናት ሁኑ፤ በአስተሳሰባችሁ ግን ጐልማሶች ሁኑ።

21. በሕግም እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤“ቋንቋቸው እንግዳ በሆነ ሰዎች፣በባዕዳንም አንደበት፣ለዚህ ሕዝብ እናገራለሁ፤ይህም ሆኖ አይሰሙኝም፤”ይላል ጌታ።

22. ስለዚህ በልሳን መናገር ለማያምኑ የሚሆን ምልክት እንጂ ለሚያምኑ አይደለም፤ ትንቢት ግን ለሚያምኑ እንጂ ለማያምኑ አይደለም።

23. እንግዲህ የቤተ ክርስቲያን ምእመናን በአንድነት በተሰበሰቡበት፣ ሁሉም በልሳን በመናገር ላይ ሳሉ፣ እንግዶች ወይም የማያምኑ ሰዎች ወደ ጉባኤው ቢገቡ፣ አብደዋል አይሉምን?

24. ነገር ግን ሁሉም ትንቢት በመናገር ላይ ሳሉ፣ እንግዳ ወይም የማያምን ሰው ቢገባ፣ በሁሉ ይወቀሣል፤ በሁሉ ይመረመራል፤

25. በልቡም የተሰወረው ነገር ይገለጣል፤ እንዲሁም፣ “እግዚአብሔር በርግጥ በመካከላችሁ ነው” በማለት በግንባሩ ተደፍቶ ለእግዚአብሔር ይሰግዳል።

26. ወንድሞች ሆይ፤ እንግዲህ ምን እንበል? በምትሰበሰቡበት ጊዜ እያንዳንዱ መዝሙር አለው፤ ትምህርት አለው፤ መግለጥ አለው፤ በልሳን መናገር አለው፤ መተርጐም አለው። ይህ ሁሉ ግን ለማነጽ ይሁን።

27. በልሳን የሚናገር ቢኖር፣ ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት በየተራ ይናገሩ፤ ሌላው ደግሞ ይተርጒም፤

28. የሚተረጒም ሰው ከሌለ ግን በጉባኤ መካከል ዝም ይበልና፤ ለራሱና ለእግዚአብሔር ይናገር።

29. ሁለት ወይም ሦስት ነቢያት ይናገሩ፤ ሌሎቹ ደግሞ የተነገረውን በጥንቃቄ ይመዝኑ።

30. ከተቀመጡትም መካከል አንድ ሰው አንድ ነገር ቢገለጥለት፣ የመጀመሪያው ተናጋሪ ዝም ይበል።

31. እያንዳንዳችሁ እንድትማሩና እያንዳንዳችሁ እንድትበረታቱ፣ ሁላችሁ በየተራ ትንቢት መናገር ትችላላችሁ።

32. የነቢያት መናፍስት ለነቢያት ይታዘዛሉ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ቆሮንቶስ 14