ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ቆሮንቶስ 10:7-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. “ሕዝቡ ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሡ” ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖት አምላኪዎች አትሁኑ።

8. ከእነርሱ አንዳንዶቹ ዝሙት ፈጽመው በአንድ ቀን ሃያ ሦስት ሺህ ሰው እንደ ረገፈ፣ እኛም ዝሙት አንፈጽም።

9. ከእነርሱ አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑና በእባብ ተነድፈው እንደ ጠፉ፣ እኛም ጌታን አንፈታተን።

10. ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳጒረመረሙና በአጥፊው እንደ ጠፉ፣ አታጒረምርሙ።

11. ይህ ሁሉ ምሳሌ ይሆን ዘንድ በእነርሱ ላይ ደረሰ፤ የዘመናት ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅም ተጻፈ።

12. ስለዚህ ተደላድዬ ቆሜአለሁ የሚል ቢኖር እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።

13. በሰዎች ሁሉ ላይ ከደረሰው የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም፤ እግዚአብሔር ታማኝ ነው፤ ስለዚህ ከምትችሉት በላይ እንድትፈተኑ አይተዋችሁም፤ ነገር ግን በምትፈተኑበት ጊዜ ፈተናውን መታገሥ እንድትችሉ፣ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።

14. ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ፤ ከጣዖት አምልኮ ሽሹ።

15. ይህን የምናገረው አስተዋይ ለሆኑ ሰዎች ነው፤ ስለምናገረው ነገር እናንተው ፍረዱ።

16. የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቈርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን?

17. እንጀራው አንድ እንደሆነ፣ እኛም ብዙዎች ሆነን ሳለ አንድ አካል ነን፤ ሁላችን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ቆሮንቶስ 10