ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 9:12-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ታላቅ ጥፋት በእኛ ላይ በማምጣት፣ በእኛና በገዦቻችን ላይ የተነገረውን ቃል ፈጸምህብን፤ በኢየሩሳሌም ላይ የተደረገውን የሚያህል ከሰማይ በታች ከቶ የለም።

13. በሙሴም ሕግ እንደ ተጻፈው፣ ይህ ሁሉ ጥፋት በእኛ ላይ ደረሰ፤ ሆኖም ከኀጢአታችን በመመለስና እውነትህን በመከተል ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ምሕረትን አልፈለግንም

14. አምላካችን እግዚአብሔር በሚያደርገው ሁሉ ጻድቅ ነውና፣ በእኛ ላይ እግዚአብሔር ጥፋት ከማምጣት አልተመለሰም፤ እኛም አልታዘዝነውም።

15. “አሁንም ሕዝብህን ከግብፅ ምድር በብርቱ እጅ ያወጣህ፣ እስከዚህም ቀን ድረስ ስምህ እንዲታወቅ ያደረግህ፣ ጌታ አምላካችን ሆይ፤ እኛ ኀጢአትን ሠርተናል፤ አንተንም በድለናል።

16. ጌታ ሆይ፤ ቀድሞ እንዳደረግኸው የጽድቅ ሥራህ ሁሉ፣ ከከተማህ ከኢየሩሳሌም፣ ከቅዱሱም ተራራህ ቊጣህን መልስ፤ በእኛ ኀጢአትና በአባቶቻችን በደል ምክንያት ኢየሩሳሌምና ሕዝብህ በዙሪያችን ባሉት ዘንድ መሣለቂያ ሆነዋል።

17. “አሁንም አምላካችን ሆይ፤ የአገልጋይህን ጸሎትና ልመና ስማ። ጌታ ሆይ፤ ስለ ስምህ ስትል ፊትህን ወደ ፈረሰው መቅደስ መልስ።

18. አምላክ ሆይ፤ ጆሮህን አዘንብለህ ስማ፤ ዐይንህን ገልጠህ መጥፋታችንንና ስምህ የተጠራበትን ከተማ ተመልከት። ልመናችንን የምናቀርበው ስለ ጽድቃችን ሳይሆን፣ ስለ ታላቅ ምሕረትህ ነው።

19. ጌታ ሆይ፤ አድምጥ! ጌታ ሆይ፤ ይቅር በል! ጌታ ሆይ፤ ስማ! አድርግም፤ ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቶአልና አምላኬ ሆይ፤ ስለ ስምህ ስትል አትዘግይ።”

20. እኔም እየተናገርሁና እየጸለይሁ፣ የራሴንና የሕዝቤን የእስራኤልን ኀጢአት እየተናዘዝሁ፣ ስለ ቅዱስ ተራራውም እግዚአብሔር አምላኬን እየለመንሁ፤

21. እየጸለይሁም ሳለሁ፣ በመጀመሪያው ራእይ አይቼው የነበረው ሰው ገብርኤል፣ በሠርክ መሥዋዕት ጊዜ በፍጥነት እየበረረ ወደ እኔ መጣ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 9