ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 8:20-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. ያየኸው ሁለት ቀንዶች የነበሩት አውራ በግ፣ የሜዶንና የፋርስን መንግሥታት ያመለክታል።

21. ጠጒራሙ ፍየል የግሪክ ንጉሥ ሲሆን፣ በዐይኖቹም መካከል ያለው ትልቁ ቀንድ የመጀመሪያው ንጉሥ ነው።

22. የተሰበረውን ቀንድ የተኩት አራቱ ቀንዶች፣ ከመንግሥቱ የሚወጡትን አራት መንግሥታት ያመለክታሉ፤ ነገር ግን በኀይል አይተካከሉትም።

23. “በዘመነ መንግሥታቸው በስተ መጨረሻ፣ ዐመፀኞች ፍጹም እየከፉ በሚሄዱበት ጊዜ፣ አስፈሪ ፊት ያለው አታላይ ንጉሥ ይነሣል።

24. እጅግ ብርቱ ይሆናል፤ ነገር ግን በገዛ ኀይሉ አይደለም። አሠቃቂ ጥፋት ይፈጽማል፤ የሚያደርገው ሁሉ ይከናወንለታል፤ ኀያላን ሰዎችንና ቅዱሳኑን ሕዝብ ያጠፋል።

25. እያጭበረበረ ይበለጽጋል፤ ራሱንም ታላቅ አድርጎ ይቈጥራል። በሰላም ተደላድለን ተቀምጠናል ሲሉ፣ ብዙዎችን ያጠፋል፤ በልዑላን ልዑልም ላይ ይነሣል፤ ይሁን እንጂ እርሱም ይጠፋል፤ ነገር ግን በሰው ኀይል አይደለም።

26. “የተሰጠህ የምሽቱና የማለዳው ራእይ እውነት ነው፤ ነገር ግን ከብዙ ዘመን በኋላ የሚሆነውን ስለሚያመለክት ራእዩን ዝጋው።”

27. እኔ ዳንኤል ዐቅሜ ተሟጦ ነበር፤ ለብዙ ቀናት ታመምሁ፤ ተኛሁም። ከዚያም በኋላ ተነሥቼ ወደ ንጉሡ ሥራ ሄድሁ። ባየሁት ራእይ ተደናግጬ ነበር፤ ነገሩም አልገባኝም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 8