ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 8:2-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. በራእዩም፣ በኤላም አውራጃ በሱሳ ግንብ ራሴን አየሁት፤ በራእዩም በኡባል ወንዝ አጠገብ ነበርሁ፤

3. ዐይኔን አንሥቼ ስመለከት እነሆ፤ ሁለት ቀንዶች ያሉት አውራ በግ በወንዙ አጠገብ ቆሞ አየሁ፤ ቀንዶቹም ረጃጅሞች ነበሩ፤ ከቀንዶቹም አንዱ ከሌላው ይረዝማል፤ የበቀለው ግን ዘግይቶ ነበር።

4. አውራ በጉም ወደ ምዕራብ፣ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ በቀንዱ ሲጐሽም አየሁ። ምንም ዐይነት እንስሳ ሊቋቋመው አልቻለም፤ ከእጁም ሊያድን የሚችል አልነበረም፤ የፈለገውን ሁሉ አደረገ፤ ታላቅም ሆነ።

5. ስለዚህም ነገር እያሰብሁ ሳለሁ፣ በዐይኖቹ መካከል ትልቅ ቀንድ ያለው አውራ ፍየል፣ መሬት ሳይነካ ምድርን ሁሉ እያቋረጠ በድንገት ከምዕራብ መጣ፤

6. በወንዙ አጠገብ ቆሞ ወዳየሁት፣ ሁለት ቀንድ ወዳለው አውራ በግ ተንደርድሮ መጣበት፤ በታላቅ ቊጣም መታው፤

7. እየወጋውና ሁለቱን ቀንዶቹን እየሰበረ፣ በጭካኔ አውራውን በግ ሲጐዳ አየሁ፤ አውራ በጉም ለመቋቋም ጒልበት አልነበረውም። ፍየሉ በምድር ላይ ጥሎ ረገጠው፤ አውራ በጉንም ከፍየሉ እጅ ለማዳን የሚችል አልነበረም።

8. ፍየሉም ታላቅ ሆነ፤ ነገር ግን በኀይሉ በበረታ ጊዜ፣ ትልቁ ቀንዱ ተሰበረ፤ በቦታውም ወደ አራቱ የሰማይ ነፋሳት የሚያመለክቱ አራት ታላላቅ ቀንዶች በቀሉ።

9. ከእነዚህም ቀንዶች መካከል በአንዱ ላይ አንድ ሌላ ትንሽ ቀንድ በቀለ፤ ወደ ደቡብ፣ ወደ ምሥራቅና ወደ መልካሚቱ ምድር በኀይል አደገ።

10. ወደ ሰማይ ሰራዊት እስኪደርስ ድረስ አደገ፤ ከከዋክብት ሰራዊትም የተወሰኑትን ወደ ምድር ጣለ፤ ረጋገጣቸውም።

11. ከሰማይ ሰራዊት አለቃ ጋር እስኪተካከል ድረስ ራሱን ከፍ ከፍ አደረገ፤ የልዑሉንም የዘወትር መሥዋዕት ወሰደበት፤ የመቅደሱንም ስፍራ አረከሰ።

12. ከዐመፅ የተነሣም የቅዱሳን ሰራዊት ከዘወትሩ መሥዋዕት ጋር ለእርሱ አልፎ ተሰጠ፤ የሚያደርገው ሁሉ ተከናወነለት፤ እውነትም ወደ ምድር ተጣለች።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 8