ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 7:4-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. “የመጀመሪያው፣ አንበሳ ይመስል ነበር፤ የንስርም ክንፎች ነበሩት፤ ክንፎቹ እስኪነ ቃቀሉ ድረስ ተመለከትሁ፤ እንደ ሰው በሁለት እግሩ እንዲቆም ከምድር ከፍ ከፍ ተደረገ፤ የሰውም ልብ ተሰጠው።

5. “እነሆም፤ ሁለተኛው አውሬ ድብ ይመስል ነበር፤ በአንድ ጐኑ ከፍ ብሎአል፤ በአፉ ውስጥ በጥርሶቹ መካከል ሦስት የጐድን ዐጥንቶች ነበሩት። እርሱም፤ ‘ተነሥ፤ እስክትጠግብ ድረስ ሥጋ ብላ!’ ተባለ።

6. “ከዚያ በኋላ ተመለከትሁ፤ በፊቴ ነብር የሚመስል ሌላ አውሬ ነበር፤ በጀርባውም በኩል የወፍ ክንፍ የሚመስሉ አራት ክንፎች ነበሩት፤ ይህ አውሬ አራት ራስ ነበረው፤ ለመግዛትም ሥልጣን ተሰጠው።

7. “ከዚህ በኋላ በሌሊት ራእይ አየሁ፤ በፊቴም የሚያስፈራና የሚያስደነግጥ በጣም ኀይለኛ የሆነ አራተኛ አውሬ ነበር፤ ትልልቅ የብረት ጥርሶች ነበሩት፤ ያደቅና ይበላ፣ የቀረውንም ሁሉ በእግሮቹ ይረጋግጥ ነበር። ከእርሱ በፊት ከነበሩት አራዊት ሁሉ የተለየ ሲሆን፣ ዐሥር ቀንዶች ነበሩት።

8. “ስለ ቀንዶቹ ሳስብ ሳለሁ፣ ከመካከላቸው አንድ ሌላ ትንሽ ቀንድ ብቅ ሲል አየሁ፤ ከመጀመሪያዎቹ ቀንዶች ሦስቱ ከፊቱ ተነቃቀሉ፤ ይህም ቀንድ የሰው ዐይኖችን የሚመስሉ ዐይኖች፣ በትዕቢትም የሚናገር አፍ ነበረው።

9. “እኔም ስመለከት፣“ዙፋኖች ተዘረጉ፤ጥንታዌ ጥንቱም ተቀመጠ፤ልብሱ እንደ በረዶ ነጭ ነበረ፤የራሱም ጠጒር እንደ ጥጥ ነጭ ነበረ፤ዙፋኑ የእሳት ነበልባል፣መንኰራኵሮቹም ሁሉ እንደሚነድ እሳት ነበሩ።

10. የእሳት ወንዝ፣ ከፊት ለፊቱ ፈልቆይፈስ ነበር፤ሺህ ጊዜ ሺሆች ያገለግሉት ነበር፤እልፍ ጊዜ እልፍ በፊቱ ቆመዋል፤የፍርድ ጉባኤ ተሰየመ፤መጻሕፍትም ተከፈቱ።

11. “ቀንዱም ከሚናገረው የትዕቢት ቃል የተነሣ፣ መመልከቴን ቀጠልሁ፤ አውሬው እስኪታረድና አካሉ ደቆ ወደሚንበለበለው እሳት እስኪጣል ድረስ ማየቴን አላቋረጥሁም።

12. ሌሎቹም አራዊት ሥልጣናቸው ተገፎ ነበር፤ ነገር ግን ለተወሰነ ጊዜና ወቅት በሕይወት እንዲኖሩ ተፈቀደላቸው።

13. “ሌሊት ባየሁት ራእይ፣ የሰውን ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመና ጋር ሲመጣ አየሁ፤ ወደ ጥንታዌ ጥንቱ መጣ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት።

14. ሥልጣን፣ ክብርና ታላቅ ኀይል ተሰጠው፤ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ መንግሥታትና ሕዝቦች ሰገዱለት፤ ግዛቱም ለዘላለም የማያልፍ ነው፤ መንግሥቱም ፈጽሞ የማይጠፋ ነው።

15. “እኔ ዳንኤል በመንፈሴ ታወክሁ፤ ያየሁትም ራእይ እጅግ አስጨነቀኝ።

16. በዚያ ከቆሙት ወደ አንዱ ቀርቤ፣ የዚህ ሁሉ እውነተኛ ትርጒም ምን እንደሆነ ጠየቅሁት።“እርሱም መለሰልኝ፤ የእነዚህንም ነገሮች ትርጒም እንዲህ ሲል ነገረኝ፤

17. ‘አራቱ ታላላቅ አራዊት ከምድር የሚነሡ መንግሥታት ናቸው፤

18. ነገር ግን የልዑሉ ቅዱሳን መንግሥቱን ይወስዳሉ፤ ለዘላለምም ይይዙታል፤ አዎን፤ ለዘላለም ይይዙታል።

19. “ከዚያም የሚያደቅቀውንና የሚበላውን፣ የቀረውንም ሁሉ በእግሮቹ የሚረጋግጠውን፣ የብረት ጥርሶችና የናስ ጥፍሮች የነበሩትን፣ ከሌሎቹ አራዊት የተለየና እጅግ አስፈሪ የሆነውን የአራተኛውን አውሬ እውነተኛ ትርጒም ማወቅ ፈለግሁ።

20. ደግሞም በራሱ ላይ ስላሉት ዐሥር ቀንዶች፣ ከመካከላቸው ብቅ ስላለው ቀንድና ከዚሁ ቀንድ ፊት ስለ ተነቃቀሉት ሦስት ቀንዶች፣ እንደዚሁም ከሌሎች ስለ በለጠው የሰው ዐይኖች የሚመስሉ ዐይኖች፣ በትዕቢትም የሚናገር አፍ ስለ ነበሩት ስለ ዚሁ ቀንድ ማወቅ ፈለግሁ።

21. እነሆም፤ ይህ ቀንድ በቅዱሳን ላይ ጦርነት ዐውጆ አሸነፋቸው፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 7